ሕወሃት የለውጡ አደናቃፊ ሳይሆን የለውጡ መሪ ነው ተባለ

(ኢሳት ዲሲ–ሕዳር 26/2011) ህዝባዊ ወያኔ ሃርነት ትግራይ/ሕወሃት/ የለውጡ አደናቃፊ ሳይሆን የለውጡ መሪ ነው ሲሉ የፓርላማው የመንግስት ተጠሪ ገለጹ።

በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ተጠሪ የሆኑትና የሕዝባዊ ወያኔ ሃርነት ትግራይ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል አቶ አስመላሽ ወልደስላሴ ከትግራይ ክልል ቴሌቭዥን ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ለውጡ በትክክል እየተተገበረ ያለውም በትግራይ ክልል ነው ብለዋል።

ለውጡ ማለት ሰላም ነው፣ ለውጥ ማለት የሕግ የበላይነት ነው ሁለቱም ተሟልተው የሚገኙት በትግራይ ክልል ነው ሲሉም ተደምጠዋል።

ከዲሞክራሲም አኳያ ካየነው እኔ እንደምረዳው ዕውነተኛው ዴሞክራሲ ያለው በትግራይ ክልል ነው ብለዋል።

ሕገ-መንግስቱ እንዳይጣስ የሚከለክል ሕዝብና ክልል እንዲሁም ድርጅት ያለው በትግራይ ነው ያሉት አቶ አስመላሽ ወልደ ስላሴ ከዚህ አንጻር የሕዉሃት የለውጥ ሃያልነቱ አያጠያይቅም ብለዋል።

በፌደራል ደረጃ እስረኞች እንዲፈቱ ሲወሰን አብረን ወስነናል አብረንም ተግብረናል ያሉት አቶ አስመላሽ ወልደ ስላሴ የፍትህ ግብረሃይል ሰብስቦ እንደነበረም አስታውሰዋል።

ባስቀመጠነው መስፈርት መፈታት ያለባቸው ሰው ያልገደሉ መሰረተ ልማት ያላወደሙ፣ በተደጋጋሚ ጥፋት ያለመፈጸሙ፣ ማህበራዊ መሰረታቸው የኛ የሆነ መሆን እንደሚገባቸው ቢገልጹም ከተባለው ውጭ እስረኞች መፈታታቸውን በቅሬታ ገልጸዋል።

የፖለቲካ ምህዳሩን የማስፋፋት ጉዳይ አቶ መለስ ከመሞታቸው በፊት የታሰበ ነው ሲሉም አቶ መለስም የለውጥ ሃይል እንደነበሩ አመልክተዋል።

አሁን በተፈጠረው ሁኔታ ይህች ሃገር የነበራት ስም እያቆለቆለ ነው ያሉት አቶ አስመላሽ ወልደስላሴ ያለፉት 27 ዓመት የጨለማ ጊዜ የሚሉ ከሃዲዎች ናቸው ብለዋል። 27ቱ ዓመት ኣንጸባረቂ ዘመን ነበር ሲሉ ገልጸዋል።

27ቱ ዓመት አንጸባራቂ ዘመን ነበር ሲሉ ገልጸዋል በዲሞክራሲም በኢኮኖሚም አንገታችንን ቀናያደረግንበት ነው ብለዋል.

ይህ በእንዲህ እንዳለም የትግራይ ክልል ከሳምንት በፊት በመቀሌና በተለያዩ የትግራይ ከተሞች ያካሄደውን ሰልፍ በመጪው ቅዳሜ በመቀሌ እንደሚደግመው ገልጿል።

የክልሉ መንግስት እንዳስታወቀው የቅዳሜው ሰልፍ በመቀሌ ብቻ የሚካሄድ ሲሆን ዓላማው በቀደመው ሰልፍ እንደነበረው ህገ-መንግስቱ ይከበር፣ መፈናቀል ይቁም የሚል እንደሆነም ተመልክቷል።