ሕወሃት እንደገና የማጥራት ስራ ይቀረዋል ተባለ

(ኢሳት ዲሲ–ጥር 10/2010)

ሕወሃት አመራሮቹን ግለሂስ እንዲያደርጉ በማድረግ እንደገና የማጥራት ስራ እንደሚቀረው የድርጅቱ ሊቀመንበር ዶክተር ደብረጺዮን ገብረሚካኤል ገለጹ።

የሕዝባዊ ወያኔ ሃርነት ትግራይ ድርጅታዊ ጉባኤ ሲጠናቀቅ በጥገኝነት ላይ የንበረውን አመራር ለማጥራት ከላይ እስከታች አሁንም ግምገማው ይቀጥላል ብለዋል ዶክተር ደብረጺዮን ገብረሚካኤል።

የድርጅቱ ነባር ታጋይ አቶ ስዩም መስፍን በበኩላቸው ሕወሃት የታገለው ከድህነት ለመውጣት ሆኖ እያል አንዳንድ አመራሮች በጥርጣሬ እንዲታይ አድርገውታል ሲሉ ተናግረዋል።

እናም አመራሩን የማጥራቱ ስራ እንደሚቀጥል አቶ ስዩም መስፍን ገልጸዋል።

ሕወሃት ሰባት ቀናትን በፈጀው ጉባኤው አስፈጻሚው ያካሄደውን ግምገማ ከከፍተኛና ዝቅተኛ ካድሬዎቹ ጋር እደተወያየበት ተገልጿል።

ከዚህ በተጨማሪ አዳዲስ ሃሳቦች ተነስተው እንደነበርም ነው የተገለጸው።

በዚሁም መሰረት ከሚቀጥለው ሳምንት ጀምሮ ግለሂስ በማካሄድ እንደገና መስመሩን የማጥራት ስራ እንደሚከናወን የድርጅቱ ሊቀመንበር ዶክተር ደብረጺዮን ገብረሚካኤል ገልጸዋል።

በዶክተር ደብረጺዮን መግለጫ መሰረት ይህ ግምገማ በሕወሃት አመራር ውስጥ አሁንም ርምጃ ለመውሰድ መታቀዱን እንደሚያመላክት ታዛቢዎች ይናገራሉ።

በሕወሃት ማጠቃለያ ጉባኤ ላይ ንግግር ያደረጉት ነባሩ ታጋይ አቶ ስዩም መስፍን በበኩላቸው በድርጅቱ አንዳንድ አመራሮች ምክንያት የጥገኝነት ችግር እንዳለ ገልጸዋል።

እናም እነዚህን የማጥራት ስራ ይከናወናል ሲሉ ተናግረዋል።

ህወሃት ለታገለለት አላማ የሚገባውን እንዳያገኝ እነዚሁ አመራሮች ምክንያት ሆነዋልም ብለዋል።

ድርጅቱ በሌላ ነገር እንዲጠረጠር ያደረጉትም እነዚሁ ናቸው ሲሉ ተናግረዋል።

ከ2 ሺ በላይ የህወሃት ካድሬዎች በተሳተፉበት የሕወሃት ጉባኤ የኢሕአዴግ አባል ድርጅቶችና የአጋር ፓርቲዎች ተወካዮች ተገኝተዋል።

እነዚሁ ተወካዮች በሕወሃት ግምገማ ተስማምተው የየራሳቸውን ሃሳብ መስጠታቸውንም ዶክተር ደብረጺዮን ተናግረዋል።

ነገር ግን በሕወሃት ድርጅታዊ ጉባኤ ላይ የደኢሕዴን ሊቀመንበር አቶ ሃይለማርያም ደሳለኝ፣ የብአዴኑ ሊቀመንበር አቶ ደመቀ መኮንንም ሆነ የአማራ ክልል ፕሬዝዳንት አቶ ገዱ አንዳርጋቸው እንዲሁም ከኦሕዴድ አመራሮች አቶ ለማ መገርሳም ሆነ ዶክተር አብይ አህመድ አልተገኙም።