ኢሳት (መጋቢት 5 ፥ 2008)
የኢትዮጵያ ልማት ባንክ በውጭ ንግድ ላይ ተሰማርተው ለሃገሪቱ የውጭ ምንዛሪን ለሚያስገኙ ተቋማት ሲሰጥ የቆየውን አነስተኛ የወለድ መጠን እንዲቀየር ሰኞ ወሰነ።
ለኩባንያዎቹ ማበረታቻው የተሰጠው ለመንግስት ገቢ የሚያደርጉትን የውጭ ምንዛሪ ለማበረታት ታስቦ የነበረ ቢሆንም፣ ሃገሪቱ የምታገኘው የውጭ ምንዛሪ እየቀነሰ በመምጣቱ ሳቢያ ማበረታቻው እንዲቀየር መደረጉን ባንኩ ገልጿል።
ለመንግስት ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ያመጣሉ የሚባሉ ድርጅቶች ከስምንት እስከ ዘጠኝ በመቶ የሚደርስ ብድር ሲፈቀድላቸው የቆየ ሲሆን ይኸው ወለድ 12 በመቶ እንዲሆን አዲስ መመሪያ መውጣቱን የባንኩ ሃላፊዎች ለሃገር ውስጥ መገናና ብዙሃን ይፋ አድርገዋል።
የባንኩ ፕሬዚደንት የሆኑት አቶ ኢሳያስ ባህረ በርካታ ኩባንያዎች በማበረታቻው ድጋፍ ሲደረግላቸው ቢቆዩም የሚገኘው የውጭ ምንዛሪ ከፍ ሊል አለመቻሉን ገልጸዋል።
በዚሁ ሂደት መንግስት ከፍተኛ ገንዘብን እንዳጣ የሚናገሩት የምጣኔ ሃብት ባለሙያዎች በበኩላቸው፣ ባንኩ የወሰደውን እርምጃ ሃገሪቱ ያጋጠማትን የውጭ ምንዛሪ እጥረት ማሳያ እንደሆነ ተናግረዋል።
በጨርቃጨርቅና በሌሎች የፋብሪካ ምርቶች ላይ ተስማርተው የቆዩ ተቋማት የውጭ ምንዛሪን እንዲያስገኙ ተብሎ አነስተኛ ወለድ ሲሰጣቸው ቢቆይም ሃገሪቱ የምታገኘው የውጭ ምንዛሪ ግን በየአመቱ እየቀነሰ መምጣቱን የልማት ባንኩ አመልክቷል።
የውጭ ምንዛሪን የሚያስገኙ ተቋማትም ከአሁን በኋላ የሚያስገኙት መጠን እየታየ የወለድ መጠኑ ላይ ማስተካከያ እንደሚገደረግላቸው የልማት ባንኩ ፕሬዚደንት አክለው ገልጸዋል።
ሃገሪቱ በ2006 አም ከውጭ ንግድ 3.2 ቢሊዮን ዶላርን አግኝታ የነበረ ሲሆን፣ ባለፈው ዓመት ገቢው ከሶስት ቢሊዮን ዶላር በታች መድረሱን ለመረዳት ተችሏል።
ባለፉት ስድስት ወራት ሃገሪቱ ከተጠበቀው በታች የውጭ ንግድ ገቢን በማስመዝገብ 1.3 ቢሊዮን ዶላር ብቻ መገኘቱን የብሄራዊ ባንክ መረጃ ያመለክታል።
ለሶስተኛ አመት መቀነስን ያሳየው የውጭ ምንዛሪ ገቢ በሃገሪቱ የኢኮኖሚ እድገት ላይ አሉታዊ ተጽዕኖን እንደሚያሳድር የምጣኔ ሃብት ባለሙያዎች አስታውቀዋል።