(ኢሳት ዲሲ–ጥር 24/2011)ኢትዮጵያዊው ሌተናል ጀኔራል ጥጋቡ ይልማ ወንድማገኝ በሶማሊያ የአፍሪካ ህብረት የሰላም አስከባሪ ሃይል (አሚሶም) አዛዥ በመሆን ተሾሙ።
ሌተናል ጀኔራል ጥጋቡ ከዚህ ቀደም በቦታው ሲያገለግሉ የነበሩትን ዩጋንዳዊውን ሌተናል ጀኔራል ሲጊይሬን በመተካት ነው የተሾሙት።
ኢትዮጵያ በአፍሪካ ሰላም በማስከበር አስተዋጽዖ መከላከያ ሰራዊቷ በተባበሩት መንግስታት ይደነቃል።
ለዚሁም በላይቤሪያ፣ በሩዋንዳ፣ በሱዳንና በሶማሊያ ያደረገችው የሰላም ማስከበር ተልዕኮ ለአብነት ይጠቀሳል።
በዚሁ ሳቢያም ኢትዮጵያዊው ሌተናል ጀኔራል ጥጋቡ ይልማ ወንድማገኝ በሶማሊያ የአፍሪካ ህብረት የሰላም አስከባሪ ሃይል (አሚሶም) አዛዥ በመሆን ተሾሙዋል።
የአፍሪካ ህብረት ልዩ መልዕክተኛ በርክክብ ስነ ስርዓቱ ላይ ሌተናል ጄኔራል ጥጋቡ የተሰጣቸው ሃላፊነት ከፍተኛ እንደሆነ እና ሃላፊነቱንም እንደሚወጡት እምነት እንዳላቸው ገልጸዋል፡፡
ሌተናል ጀኔራል ጥጋቡ ይልማም የተሰጣቸው ተልዕኮ ፈታኝ ቢሆንም ከዳር እንደሚያደርሱት መናገራቸው ከአሚሶም የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
ሌተናል ጀኔራል ጥጋቡ ከትናንት ጀምሮ ስራ መጀመራቸው ነው የተነገረው።
በኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ውስጥ ለ34 ዓመታት በተለያዩ ዘርፎች ማገልገላቸው ተገልጿል።
ስራቸውን በጀመሩበት ወቅት ባደረጉት ንግግርም የተሰጣቸው ተልዕኮ ፈታኝ ቢሆንም ከዳር እንደሚያደርሱት ተናግረዋል።
በትምህርት ዝግጅታቸው በቢዝነስ አድሚኒስትሬሽን ሁለተኛ ዲግሪ፣ በሊደርሺፕ እና በወታደራዊ ሳይንስ ደግሞ የመጀመሪያ ዲግሪ እንዲሁም በህግ ዲፕሎማ አላቸው።