ላለፉት አስር ቀናት ሲካሄድ የሰነበተው የአገር ቤቱ ቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ተጠናቀቀ

ጥቅምት ፳፪ (ሀያ ሁለት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-ቅዱስ ሲኖዶሱ በርካታ ጉዳዮችን አንስቶ በጥልቀት በመዳሰስ ልዩ ልዩ ውሳኔዎችን ያሳለፈ ሲሆን፤ በአገር ቤትና እንዲሁም በውጭ አገር በሚገኘው ቅዱስ ሲኖዶስ መካከል በመጪው ኅዳር ወር በዳላስ ቴክሳስ ለሚካሄደው የዕርቀ ሰላም ውይይት አስመልክቶ የቅዱስ ሲኖዶሱ ልኡክ መደራደሪያ ናቸው የተባሉ አምስት ነጥቦች ለይቶ ማስቀመጡን ደጀ ሰላም ድረ ገጽ ዘግቧል።

እነኚህም አምስቱ ነጥቦች “የሰላምና አንድነት ጉባኤው” ላቀረባቸው ሰባት ጥያቄዎች በተሰጡ መልሶች ላይ በመመሥረት የተዘጋጁ መኾናቸውን ምንጮቹን ጠቅሶ የዘገበው ደጀ ሰላም፤ ከሰባቱ “የሰላምና አንድነት ጉባኤው” ጥያቄዎች መካከል “ብሔራዊ ዕርቅ”ን አስመልክቶ የቀረበው “ከዕርቀ ሰላሙ አጀንዳ ጋራ ግንኙነት የለውም” በሚል ተቀባይነት እንዳላገኘ አስታውቋል።

በስደት የሚገኙትን የቤተክርስቲያኗ ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስን በተመለከተም “በመረጡት ስፍራ በጸሎት ተወስነው ሲኖሩ መንበረ ፓትርያርኩ ደግሞ ደመወዝ፣ መኖሪያ ቤት፣ ተሽከርካሪና ሌሎችንም አስፈላጊ ነገሮች በማሟላት የደኅንነት ጥበቃም ያደርግላቸዋል፡፡” የሚል ውሳኔ ተላልፎአል።

 

ደጀ ሰላም ይህንኑ አስመልክቶ ምንጮቹን ጠቅሶ እንደዘገበው ከሆነ፣ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ “በጸሎት ተወስነው በመረጡት ስፍራ ይኑሩ” ሲባል በሕገ ቤተ ክርስቲያን ለፓትርያርኩ በተሰጠው ሥልጣንና ተግባር መሠረት÷ በመንበረ ፓትርያርኩ እየተገኙ የቅዱስ ሲኖዶሱን ስብሰባ በርእሰ መንበርነት መምራትና ውሳኔዎቹን ማስፈጸምን፤ በቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ መሠረት ኤጲስ ቆጶሳትን፣ የታላላቅ አድባራትና ገዳማት አለቆችንና አበምኔቶች መሾምን፤ በውጭ ግንኙነት ቤተ ክርስቲያንን መወከልን. . . ሊያካትት አይችልም። ይህም የቅዱስ ሲኖዶሱ ምልአተ ጉባኤ አዝማሚያ የቅዱስነታቸውን ፈቃድ ባካተተ መልኩ ወደ ስድስተኛው ፓትርያርክ ሹመት የሚያንደረድር ነው በማለት ስጋቱን ገልጿል።

ከአቡነ ጳውሎስ እረፍት በኋላ ለቤተ ክርስቲያኗ ሰላምና አንድነት ሲባል በአባቶች መካከል የተፈጠረው መለያየት እንዲቀርና ብፁዕ አቡነ መርቆርዮስ ወደ መንበራቸው ተመልሰው የተጣሰው ቀኖና ቤተ-ክርስትያን እንዲከበር ከምንጊዜውም በበለጠ ጥረት እየተደረገ ቢሆንም፣ የኢሕአዴግ መንግስት ግን ሌላ ፓትርያርክ ይመረጥ ዘንድ በወኪሎቹ አማካኝነት ቅዱስ ሲኖዶሱ ላይ ከፍተኛ ጫና እያደረገ ይገኛል።

ዛሬ የተጠናቀቀው የቅዱስ ሲኖዶሱ ጉባዔ በተጨማሪም፦ በአምስተኛው ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ የተሾሙ 49 ጳጳሳት በስደት በሚገኙት አባቶች ዘንድ ተቀባይነት እንዲያገኙ፣ በአንጻሩም በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ በስደት የተሾሙት 13 ጳጳሳት በቅዱስ ሲኖዶሱ ዘንድ ዕውቅናና ተቀባይነት እንዲያገኙ አቋሙን ማስቀመጡ ታውቋል።

በውጭ አገር የሚገኘው ሲኖዶስ በአገር ውስጥ የሚገኘው ሲኖዶስ ያስተላለፈውን ውሳኔ ይቀበለው አይቀበለው እስካሁን የታወቀ ነገር የለም።