ሊሰበሰብ ከታቀደው የውጭ ንግድ ገቢ ግማሽ ያህሉ ብቻ መገኘቱ ተገለጸ

ኢሳት (ሰኔ 1 ፥ 2008)

በመገባደድ ላይ ባለው የ2008 በጀት አመት ከውጭ ንግድ ገቢ ሊገኝ ከታቀደው አራት ቢሊዮን ዶላር ውስጥ ባለፉት ዘጠኝ ወራቶች 51 በመቶ የሚሆነው ብቻ መገኘቱን የንግድ ሚኒስቴር ገለጸ።

የውጭ ንግድ ገቢ ማሽቆልቆል የሃገሪቱ የንግድ ሚዛን ከ16 ቢሊዮን ዶላር በላይ ልዩነት እንዲያሳይ ምክንያት መሆኑም ታውቋል።

ባለፉት ዘጠኝ ወራቶች የተገኘው የውጭ ንግድ ገቢ ካለፈው አመት ጋር ሲነጻጻር በ 6.5 በመቶ ቅናሽን ያሳየ ሲሆን፣ የንግድ ገቢው ማሽቆልቆል በሃገሪቱ የውጭ ምንዛሪ ክምችትና በኢኮኖሚ እድገቱ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ማሳደሩን የምጣኔ ሃብት ባለሙያዎች ገልጿል።

ጉዳዩ ለመንግስት አሳሳቢ እየሆነ መጥቷል ሲል የገለጸው የንግድ ሚኒስቴር የኢትዮጵያ የንግድ ሚዛን ለመጀመሪያ ጊዜ ከ 16 ቢሊዮን ዶላር በላይ ልዩነት ማሳየቱን አስታውቋል።

በቀጣዮቹ ሶስት ወራቶች ውስጥ ከውጭ ንግድ ገቢ የሚገኘው ገንዘብ ሊገኝ የታቀደው የውጭ ምንዛሪ ሊሳካ የማይችል በመሆኑም የዘንድሮው በጀት የንግድ ገቢ በከፍተኛ መጠን ማሽቆልቆሉን ያስመዘግባል ተብሎ ተሰግቷል።

በመገባደድ ላይ ባለው የ2008 ዓም መንግስት ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ ድጋፍ ይገኛል ብሎ የነበረ ቢሆንም ሊገኝ የቻለው 290 ሚሊዮን ብር አካባቢ ብቻ መሆኑ ታውቋል።

በተያዘው አመት የተገኘው የበጀት ድጋፍ ካለፈው አመት ጋር ሲነጻጸር በ90 በመቶ አካባቢ አንሶ መገኘቱን የንግድ ሚኒስቴር አስታውቋል።

በተያዘው በጀት አመት በተጨማሪ እሴት ታክስ ከ16 ቢሊዮን ብር በላይ ለመሰብሰብ እቅድ ቢያዝም ባለፉት ዘጠኝ ወራቶች መሰብሰብ የተቻለው 51 በመቶ አካባቢ ብቻ መሆኑን የንግድ ሚኒስቴር ሰሞኑን ለፓርላማ ያቀረበው መረጃ ዋቢ በማድረግ በሃገር ውስጥ ያሉ መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።

የተጨማሪ እሴት ገቢ ካለፈው አመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸት በ23 በመቶ አሽቆልቁሎ መገኘቱን ለመረዳት ተችሏል።

በተያዘው በጀት አመት ሃገሪቱ በተለያዩ ዘርፎች አጋጥሟታል የተባለው የንግድ እንቃቃሴ መዋዠቅ በአጠቃላይ ኢኮኖሚያዊ መቀዛቀዝን ሊያስከትል እንደሚችል የምጣኔ ሃብት ባለሙያዎች በመግለጽ ላይ ናቸው።