ግንቦት ፭ (አምስት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:- “ሉሲ መውጣት የለባትም”የሚል አቋም ይዘው የነበሩ ወገኖች፤ በአቶ መለስ ደብዳቤ ተረትተው ሉሲ እንድትወጣ መደረጉም ተጠቁሟል።
ላለፉት አምስት ዓመታት አሜሪካ ከርማ የተመለሰችው ሉሲ ከአንድ ዓመት በላይ መቆየት እንዳልነበረባት ኢትዮጵያዊው የቅሬተ አካል ሳይንቲስት ዶ/ር ዘረሰናይ ዓለምሰገድ መናገራቸውን ሪፖርተር ዘገበ።
ዶክተር ዘረሰናይ ይህን ያሉት፤የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን ሚያዝያ 30 ቀን 2005 ዓ.ም. በብሔራዊ ሙዚየም ባዘጋጀው የ“እንኳን ደህና መጣሽ” ዝግጅት ላይ ነው።
ዶክተር ዘረሰናይ በሉሲ የአሜሪካ ቆይታ ደስተኛ አለመሆናቸውን አስረግጠው የተናገሩት፤ሉሲ በዓለም ታዋቂ በሆኑት የአሜሪካ ስሚዘንያንስ ሙዚየምና የኒውዮርኩ የአሜሪካ የተፈጥሮ ታሪክ ሙዚየም ውስጥ የመታየት ዕድል ተነፍጓት በተወሰነ ቦታ ብቻ ለዚያን ያህል ጊዜ እንድትቀመጥ መደረጓ አግባብ አለመሆኑን በመግለጽ ነው፡፡
እንደ ዶክተር ዘረሰናይ ገለፃ ሉሲን ከአንድ ዓመት ባልበለጠ የጊዜ ገደብ ውስጥ አሳይቶ መመለስ ይቻል ነበር፡፡
ጋዜጣው እንዳለው እንደ ዶ/ር ዘረሰናይ ሁሉ ደስተኛ አለመሆናቸውን የተናገሩት ሌላው ሳይንቲስት ደግሞ፤ ከ38 ዓመት በፊት በአፋር- ሀዳር ሉሲን ያገኟት አሜሪካዊው ዶናልድ ጆሃንሰን ናቸው፡፡
በሉሲ የውጭ ጉዞ ጥንስስ ወቅት ሳይንቲስቶችና ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት የ“ትውጣ” “አትውጣ” እሰጣ አገባ ውስጥ ገብተው እንደነበር ያስታወሱት ዶ/ር ዘረሰናይ፣ ሳይንሳዊ የሆነ ምክንያት በማስቀመጥ “አትውጣ’ የሚል አቋም የያዘው ብዙሀኑ የባለሙያዎች ቡድን ፤ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር በፃፉት ደብዳቤ መረታቱንና ቅሬተ አካሉ በግንቦት 1999 ዓ.ም. ለጉብኝት እንዲወጣ መወሰኑን አስታውሰዋል፡፡
ከስድስት ዓመት በፊት ሉሲ ወደ አሜሪካ እንድትጓዝ መንግሥት በወሰነበት ወቅት የዘርፉ ባለሙያዎች፣ በዩኔስኮ በ20 ሳይንቲስቶች የተፈረመውን “ማንኛውንም ዓይነት ጥንተ ሰው ቅሬተ አካል ለሳይንሳዊ ሥራዎች ካልሆነ በቀር ከተገኘበት አገር ውጭ እንዳይንቀሳቀስ” የሚለውን ድንጋጌ ይፃረራል የሉሲን ጉዞ መቃወማቸው አይዘነጋም።
የ3.2 ሚሊዮን ዓመት ዕድሜ ያላት ሉሲ (ድንቅነሽ) በሰላም ብትመለስም፣ ከቆይታዋ መርዘም አኳያ ተገኘ የተባለው ገቢ ያን ያህል አስደሳች አለመሆኑም በመድረኩ ተንፀባርቋል፡፡
በሉሲ የአሜሪካ ቆይታ ተገኘ የተባለው የገንዝብ መጠን 1.5 ሚሊዮን ዶላር እንደሆነ በገባችበት ዕለት ቢነገርም የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተሩ አቶ ዮናስ ደስታ ግን አጠቃላይ የፋይናንስና ሌላው ሪፖርት ገና ተዘጋጅቶ ያላለቀ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ኢሳት የሉሲን መጓዝ አስመልክቶ የተነሱትን ቅሬታዎች በወቅቱ ሲያቀርብ መቆየቱ ይታወሳል።