ለ3ቀናት የተጠራው በቤት ውስጥ የመቀመጥና የስራ ማቆም አድማ ተጀመረ

(ኢሳት ዲሲ–የካቲት 26/2010)

ህገወጡን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በመቃወም ለ3ቀናት የተጠራው በቤት ውስጥ የመቀመጥና የስራ ማቆም አድማ በመላው የኦሮሚያ ክልል በመካሄድ ላይ ነው።

በአዲስ አበባ ዙሪያ በምዕራብ ሸዋ፣ በወለጋ፣ በሀረርጌ፣ በአርሲ፣ በባሌና በሌሎች አካባቢዎች ዛሬ የተጀመረው አድማ የንግድና የትራንስፖርት እንቅስቃሴውን ሙሉ በሙሉ እንዲቋረጥ ማድረጉ ታውቋል።

በአዲስ አበባ አውቶቦስ ተራዎች ጭር ብለው ውለዋል።

ከጅማ ወደ አዲስ አበባ በወታደራዊ አጀብ እየመጣ ያለ የህዝብ ማመላለሽ አውቶቡስ አሰንዳቦ ላይ ጥቃት ደርሶበታል።

በርካታ መንገዶች በመዘጋታቸው ወደ አዲስአበባ የሚመጡ ተሽከርካሪዎች መንቀሳቀስ እንዳልቻሉ ታውቋል።

ከአዲስ አበባ ጀምሮ በአራቱም አቅጣጫዎች በሚገኙ የኦሮሚያ ክልል ከተሞች አድማው ሙሉ በሙሉ መመታቱን መረጃዎች አመልክተዋል።

በአዲስ አበባ ዙሪያ በለገጣፎ፣ ቡራ፣ ሰበታ፣ ፉሪ፣ ዓለምገናና ሌሎች የኦሮሚያ ልዩ ዞን ከተሞች አድማው በስፋት ከተመታባቸው አካባቢዎች የሚጠቀሱ ናቸው።

በወሊሶ መስመር እስከጅማ ድረስ ባሉ ከተሞች አድማው በተጠናከረ ሁኔታ በመካሄድ ላይ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል።

ዛሬ የአዲስ አበባ አውቶቡስ ማቆሚያዎች ጭር ብለው እንደዋሉም የደረሰን መረጃ አመልክቷል።

በቤት ውስጥ መቀመጥና የስራ ማቆም አድማው በጂማና አጋሮ ከትላንት ጀምሮ መመታቱን መረጃዎች ያመለክታሉ።

ትላንት ጅማ በርካታ ሱቆችና መደብሮች የተዘጉ ሲሆን ዛሬ ቀሪዎቹ ተቀላቅለው አድማው ሙሉ በሙሉ በመካሄድ ላይ መሆኑ ታውቋል።

ምዕራብ ኢትዮጵያ ሙሉ በሙሉ አድማ እየተካሄደ መሆኑንም የሚያመለክቱ መረጃዎች ለኢሳት ደርሰውታል።

በመቱ ዛሬ ሱቆችና መደብሮች ተዘግተዋል። የትራንስፖርት አገልግሎት ተቋርጧል።

ትላንት ከአዲስ አበባ የወጡ የህዝብ ማመላለሺያና ሌሎች ተሽከርካሪዎች በጊቤ በረሃ አበንቲ በሚባል ቦታ እንዲቆሙ ተደርገዋል።

በወታደራዊ ጥበቃ ከጅማ የተነሳ አንድ የህዝብ ማመላለሺያ አውቶቡስ አሰንዳቦ ከምትባል አነስተኛ ከተማ ሲደርስ በህዝብ በተወሰደበት ርምጃ መስታወቱ መሰባበሩ ታውቋል።

በመንገደኞች ላይ የደረሰ ጉዳት እንደሌለም ተገልጿል።

በምዕራብ ሸዋ ባለፈው ቅዳሜ የተጀመረው አድማ የቀጠለ ሲሆን በአምቦ፣ ጉደርና ጊንጪ የንግድና የትራንስፖርት አገልግሎት ተቋርጧል። ዋና ዋና መንገዶች ተዘግተዋል።

በወለጋም በበርካታ ከተሞች አድማ እየተካሄደ ነው። በጊምቢና ነጆ የተጠናከረ ሲሆን ነቀምትም ከእንቅስቃሴ ውጪ ሆና ውላለች።

በምስራቅና ምዕራብ ሀረርጌም በተመሳሳይ የስራ ማቆምና በቤት ውስጥ የመቀመጥ አድማ ተደርጓል።

ከአዲስ አበባ ወደ ድሬዳዋ የሚወስደው መንገድ የተዘጋ ሲሆን የመከላከያ ሰራዊት መንገዱን ለማስከፈት እየሞከረ መሆኑን የደረሰን መረጃ ያመለክታል።

በሌላ በኩል የህዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪዎች ስራ እንዲጀምሩ ሾፌሮች በወታደሮች እየተገደዱ መሆኑን ለኢሳት በደረሰ መረጃ ላይ ተመልክቷል።

ሾፌሮቹ ግን ዋስትና የለንም በማለት ማስፈራሪያውን አልተቀበሉትም።

በተያያዘ ዜና ወልቂጤም አድማውን በመቀላቀል ከእንቅስቃሴ ውጭ ሆና መዋሏ ታውቋል።

ከሳምንት በፊት ለ8ቀናት የቆየ አድማ በመታችው ወልቂጤ ዛሬም ንግድ ቤቶች ተዘግተው እንደነበር ተገልጿል።

አንድ ታንክ ወልቂጤ ከተማ ላይ መታየቱን የገለጸው ወኪላችን ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የአጋዚ ወታደሮችም ወደ አካባቢው መሰማራታቸውን ጠቅሷል።

በሌላ በኩል ከአድማው ጋር በተያያዘ በጅጅጋ የንግድ እንቅስቃሴው በመቋረጡ ህዝቡ በምግብ እጥረት ችግር ላይ መውደቁን ለማወቅ ተችሏል።

በዚህም ከፍተኛ የኢኮኖሚ ቀውስ መፈጠሩም ታውቋል።