ለ10ኛው የብሔረሰቦች ቀን የምግብ መስተንግዶ 12 ሚሊዮን ብር መከፈሉ ታወቀ

(ኢሳት ዲሲ–ሰኔ 8/2010) በጋምቤላ ክልል በ2008 ተካሂዶ ለነበረው 10ኛው የብሔር ብሔረሰቦች ቀን የምግብ መስተንግዶ ወይዘሮ ትልቅ ሰው ገዳሙ ለተባሉ የሆቴል ባለቤት ከክልሉ የመጠባበቂያ በጀት 12 ሚሊዮን ብር መከፈሉ ተገለጸ ።

ገንዘቡ በበአሉ አስተባባሪ ጽህፈት ቤት አቶ ማትዮስ ገለታ ስም ወጭ ተድርጎ ለወይዘሮ ትልቅ ሰው ገዳሙ እንዲከፈል ትእዛዝ የሰጡት የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጋትሉክ ቱት  ናቸው።

የጋምቤላ ምክር ቤት ታመው ለሚገኙት የክልልሉ መስተዳድር አቶ ጋትሎክ ቱት መታከሚያ በቅርቡ ከ 1ሚሊዮን ብር ባላይ ወጭ እንዲደረግ መፍቀዱም ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች በዓል በዳንኪራና በፈንጠዝያ በየአመቱ የሚከበር በዓል ነው። ክልሎች በየተራ በሚያከብሩት በዚህ በዓል የሕዝብና የሀገር ሀብት በእጅጉ እንደሚባክን ሲነገር ቆይቷል።

8 ሚሊዮን ዜጎች በድርቅ ሳቢያ የምግብ እጥረት አጋጥሟቸው የእርዳታ ያለህ በሚባልበት  በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ የጋምቤላ ክልል በ10ኛው የብሄር ብሄረሰብ በዓል ለሚታደሙ 2ሺህ እንግዶች ግብዣ 12 ሚሊዮን ብር ወ/ሮ ትልቅ ሰው ገዳሙ ለተባሉ የሆቴል ባለቤት ተከፍሏል።

ለአንድ ቀን ለሚከበር በዓል ለአንድ እንግዳ ብቻ በነፍስ ወከፍ ለምግብ ብቻ 6ሽህ ብር ተከፍሎ ለ2ሽህ ሰው 12 ሚሊዮን ብር ከክልሉ የመጠባበቂያ በጀት እንዲከፈል ተደርጓል። በጋምቤላ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጋትሉክ ቱት ለክልሉ ፋይናንስና ኢኮኖሚ ልማት ቢሮ ገንዘቡ እንዲከፈል የተፃፉት ደብዳቤ እንደሚያመለክተው ለመስተንግዶ ሲባል ለወ/ሮ ትልቅ ሰው ቅድሚያ ክፍያ 2 ሚሊዮን 2 መቶ ሺህ ብር ተከፍሏል። ቀሪውን ክፍያ አስመልክቶ ጥር 17 2008  ዓ/ም  የተሰበሰብው ካቢኔ 9 ሚሊዮን 8 መቶ ሺህ ብር ለወ/ሮ ትልቅ ሰው ገዳሙ ከመጠባበቂያ በጀት ወጭ ሆኖ ኣንዲከፈል ወስኗል። በቅርቡም የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳደር ለሆኑት አቶ ጋትሉክ ቱት የሕክምና ወጭ ከክልሉ መጠባበቂያ በጀት ከ1ሚሊዮን ብር በላይ እንዲከፈል መወሰኑ ይታወሳል።

በባህርዳር የግራንድ ሆቴል ባለቤት እንደሆኑ የሚነገርላቸው ወ/ሮ ትልቅ ሰው ገዳሙ በጋምቤላም ባለ 5 ኮከብ ተመሳሳይ ሆቴል አላቸው። ው/ሮ ትልቅ ሰው ገዳሙ በባህርዳርም ሆነ በጋምቤላ ያላቸውን ሆቴሎች ጨምሮ በትራንስፖርት ንግድ በመሰማራት ከፍተኛና በርካታ የጭነት መኪናዎች እንዳላቸውም ይታወቃል። ከተራ ውስኪ ቤት ባለቤትነት ተነስተው ከፍተኛ ሀብት የካበቱት ወ/ሮ ትልቅ ሰው ገዳሙ ከብአዴን ባለስልጣናት እና ከቀድሞው የልማት ባንክ  ሃላፊዎች ጋር ቅርበት እንዳላቸው ይነገራል።