ለፕሬስ ነፃነት ማንኛውንም መስዋትነት እንከፍላለን! ሲሉ የፍትህ ጋዜጠኞች ተናገሩ፡፡

ሐምሌ ፲፱ (አስራ ዘጠኝ) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:- የፍትህ ዋና አዘጋጅ የሆነው ተመስገን ደሳለኝ ዛሬ ባወጣው ጽሁፍ ” ነገም ፍትህ እንደወትሮዋ በመላ ኢትዮጵያ ጎዳናዎች አትነግስም፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ቤት ነው፡፡ በማለት ችግሩን እንደሚከተለው ዘርዝሯል።
“ነገሩ እንዲህ ነው፡- ዛሬ ረፋዱ ላይ የፍትህ ጋዜጣ ሽያጭ ክፍል ሰራተኞች ማታ ወደማተሚያ ቤት ለምትገባው ጋዜጣችን ክፍያ ሊፈፅሙ ሄዱ፡፡ የማተሚያ ቤቱ ሃላፊ ደግሞ ‹‹ማኔጅመንቱ ፍትህን ላለማተም ወስኗል›› አሉና አቋማቸውን ተናገሩ፡፡ ይህን ጊዜም ከአንድ ባልደረባዬ ጋር ወደ ማተሚያ ቤቱ አመራሁ፡፡ ሃላፊውንም ለምን አላትምም እንዳሉ ስጠይቃቸው ” እንዴ ባለፈው የታገደው ጉዳይ ስላላለቀ ነው” ሲሉ ፣ ይህ እንደማይመለከታቸው ስነግራቸው ደግሞ ” ፍትህ ሚኒስቴር በቃል እንዳታትሙላቸው ብሎናል” እያሉ በሀፍረት ተሸማቀው አሸማቀቁን። እኛም እንደፈረደብን ፍትህ ሚ/ር ግቢ ሄድን ። ሆኖም እስከ 10 ሰአት ድረስ የሚያነጋግረን ሀላፊ አጣን። ሁሉም እኔን አይመለከተኝም በሚል ሀላፊነት ሊወሰድ አልፈለገምና; በመጨረሻ ሚኒሰቴሩ ቢሮ ገብተን ” ካላነጋገሩን አንወጣም ስንል” ሚኒሰቴር ዲኤታው እንዲያነጋግሩን ተደረገ። ሚኒስትር ዴታውም ዘና ብለው እገዳው የታዘዘው በእኔ ስር ነው፣ ይህን ሳምንት ግን አታትሙ አላልንም።” አሉን።

ተመስገን እንዳለው ይህንኑ ለማስረዳት ወደ ብርሀንና ሰላም ቢያመሩም፣ ሀላፊዎች የመውጫ ሰአት ስለደረሰ ሁሉም ወጥተዋል። ፍትህም ሳትታም አደራለች።

በመጨረሻም ” የጀመርነውን ትግል የትኛውንም መስዋትነት ከፍለን ከዳር እናደርሰዋለን” በማለት ተመስገን ሀሳቡን ጽሁፉን አጠቃሏል።

አለማቀፉ የጋዜጠኞች መብት ተንከባካቢ ድርጅት ( ሲፒጄ) በፍትህ ጋዜጣ ላይ የተወሰደውን እርምጃ ማውገዟ ይታወሳል።

_____________________________________________________________________________________________

ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.

ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide