ለጤናና ስፖርት እየተባለ ከፌደራል ፖሊስ አባላት የሚቆረጠው ገንዘብ እንዲሁም የውጭ ድርጅቶች ለጥበቃ እያሉ የሚከፍሉት ገንዘብ እየተዘረፈ መሆኑን አንድ በሚስጢር የተያዘ  የምርመራ ሰነድ አመለከተ

ከሰራዊቱ የሚደርሰው ጥቆማ ለመንግስት ህልውና አደጋ እየፈጠረ መምጣቱን ተከትሎ በተደረገው ማጣራት ከፌደራል ፖሊስ አባላት ለጤና እየተባለ የሚቆረጠው ገንዘብ ከጤና ጋር ግንኙነት ለሌላቸው የህወሃት ፣ የኢህአዴግ በአላት እና ለመሳሰሉት ወጪ እንደሚደረግ በኮማንደር እሸቱ የሮማው፣ በኮማንደር አበበ ኪ.ማርያም፣ በ ኮማንደር ደጄኔ ወንድሜነህ፣ በም/ኮማንደር ደነቀው ክፍሌ እንዲሁም ም/ኢ/ር ተሾመ ጊዳ የተደረገው የምርመራ ሪፖርት ያመለክታል።

እንዲሁም ኢሲኤ፣ ቻይና፣ ግለገል ጊቤ፣ ካጅማ እና ከመሳሰሉት የውጭ አገር እና የአገር ውስጥ ተቋማት ለጥበቃ በሚል ለፌደራል ፖሊስ የሚሰጠው በሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ እንዲሁም በኮንትሮባንድ የሚወረሰው ገንዘብ  በግል አካውንት የሚገባ እና ኦዲት ተደርጎ የማያውቅ መሆኑን የምርመራ ሪፖርቱ ያመለክታል።

ረ/ ኮ/ር አለምጸሃይ ካሳና ም/ኮ/ሲሳይ ሽኩር ከሰራዊቱ ለጤና እየተባለ ከሚዋጣው ገንዘብ አለ ሰራዊቱ እውቅና 700 ሺ ብር በማውጣታት ታክመው መውጣታቸውም በምርምራ ሪፖርቱ ተረጋግጧል።