(ኢሳት ዲሲ–ጥር 2/2010)
የአሜሪካው ኮንግረስማን ማይክ ኮፍማን በአሜሪካ በሚኖሩ ተቃዋሚዎችና ጋዜጠኞች ላይ የሚደረገው የስለላ ተግባር እንዲቆም በማሳሰብ ለውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሬክስ ቲለርሰን ደብዳቤ መጻፋቸው ታወቀ።
ኮንግረስማን ኮፍማን የህወሃት አገዛዝ በውጭ በሚኖሩ ተቃዋሚዎችና ጋዜጠኞች ላይ የሚያደርገው የኢንተርኔት የስለላ ተግባር እየተጠናከረ በመምጣቱ አሜሪካ ርምጃ እንድትወስድ ጠይቀዋል።
የኮሚፕውተር ቫይረስ በማሰራጨት የስለላ ተግባር ለመፈጸም በሚሊየን የሚቆጠር ገንዘብ ወጪ የሚያደርገውን የህወሃት አገዛዝ ተጠያቂ በማድረግ አሜሪካ ለቆመችለት መርህ እንድትገዛም ኮፍማን አሳስበዋል።
የህወሃት አገዛዝ በብዙ ሚሊየን ዶላር ግዢ ዘመናዊ የስለላና የማፈኛ መሳሪዎችን በመግዛት መጠነ ሰፊ ዘመቻ የከፈተው ከሶስት ዓመት በፊት ጀምሮ ነው።
ኢሳትን ጨምሮ አገዛዙ ላይ ትችት የሚያቀርቡ መገናኛ ብዙሃን ላይ ተደጋጋሚ የስለላ ተግባር መፈጸሙ ተጋልጧል።
ሲትዝን ላብ የተሰኘው መቀመጫውን ካናዳ ያደረገው ተቋም እንዳጋለጠው የህወሀት አገዛዝ የኮምፒውተር ቫይረስ በኢሜይልና ስካይፕ መልክዕቶች ጋር የሚልከው በተለይም በአገዛዙ ላይ የተለየ አቋምና አመለካከት ባላቸው ጋዜጠኞች፣ አክቲቪስቶችና የፖለቲካ መሪዎች ላይ ነው።
ይህንንም የስለላ ተግባር ለሚያከናውኑ ኩባንያዎች በብዙ ሚሊዮን ዶላር የሚቆጠር ገንዘብ ይከፍላል።
በዓለም ላይ በውጭ የሚኖሩ ዜጎቻቸውን በመሰለል ግንባር ቀደም ከሚባሉ ሀገራት አንዷ ኢትዮጵያ መሆኗን የሰብዓዊ መብት ተቆርቋሪዎች ይገልጻሉ።
የአሜሪካ ምክርቤት አባል የሆኑት የኮሎራዶው ኮንግረስ ማን ማይክ ሆፍ ማን ይህ ጉዳይ በእጅጉ ያሳሰባቸው መሆኑን ለአሜሪካን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በጻፉት ደብዳቤ ላይ ገልጸዋል።
ኮንግረስማን ማይክ ሆፍ ማን እንዳሉት የኢትዮጵያ መንግስት በአሜሪካ በሚኖሩ የተቃዋሚ አባላትና ጋዜጠኞች ላይ የሚያደርገው የተነጣጠረ የስለላ ተግባር በእጅጉ የሚያሳስብ ነው።
ማይክ ሆፍማን ለውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሬክስ ቲለርሰን በጻፉት ደብዳቤ የኢትዮጵያው አገዛዝ ለሚፈጽማቸው የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ሃላፊነቱን እንዲወስድና በተቃዋሚዎችና አክቲቪስቶች ላይ የሚያደረገውን የኢንተርኔት ስለላ እንዲያቆም አሜሪካ አስፈላጊውን ጫና እንድትፈጥር ጠይቀዋል።
ማይክ ሆፍማን በደብዳቤያቸው የኢትዮጵያው አገዛዝ ከ20 በላይ ሀገራት ውስጥ በሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ተቃዋሚዎችና ጋዜጠኞች ላይ ለሚያደርገው የስለላ ተግባር ከፍተኛ የሆነ ገንዘብ እንደሚያወጣ ጠቅሰዋል።
ሆፍማን እሳቸው በወከሉት የኮሎራዶ ግዛት ነዋሪ የሆነ ኢትዮጵያዊ የዚሁ የኮምፒውተር ቫይረስ ጥቃት ሰለባ መሆኑን ጠቅሰው ጉዳዩ በጥልቅ ያሳስበኛል ብለዋል።
የኮምፒወተር ቫይረስ በአፋኝ አገዛዞች በቀላሉ ከገበያ ላይ የሚገኝ በመሆኑ የነጻነትና ዲሞክራሲ ታጋዮች ለጥቃት የተጋለጡ መሆናቸውንም በማስታወስ የኢትዮጵያው አገዛዝ ከሚያስተዳድረው ሀገር ውጭ የሚፈጽመውን የስለላ ጥቃት በአስቸኳይ እንዲያቆም መደረግ አለበት ሲሉ ለውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ በጻፉት ደብዳቤ ላይ አሳስበዋል።