(ኢሳት ዲሲ–ሰኔ 22/2010) ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ የጀመርነውን ለውጥ ወደኋላ የሚቀለብስ ማንኛውንም ነገር ለመሸከም ዝግጁ አይደለንም ሲሉ ገለጹ።
90 በመቶ የሚሆኑት የኢሕአዴግ አባላት የለውጥ ጉዞውን ደግፈው መቆማቸውንም አስታውቀዋል።
ኢትዮጵያ ወደነበረው የጭንቀት ጊዜ እንዳትመለስ መከፈል የሚገባው ዋጋ ሁሉ እንደሚከፈልም ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ ተናግረዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ ይህንን የተናገሩት አፋር ክልል ሰመራ ላይ ከአካባቢው ነዋሪዎች ጋር ባደረጉት ውይይት ነው።
90 በመቶ የኢሕአዴግ አባላት በለውጡ ውስጥ ተሳታፊ ሆነዋል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ መጥራት የሚገባውን እያጠራን እንሄዳለን።
የጀመርነውን የለውጥ ጉዞ ለመቀልበስ የሚደረገውን ማንኛውንም ነገር ለመሸከም ግን ዝግጁ አይደለንም ብለዋል።
“ኢሕአዴግ ውስጥ ለውጥ መጥቷል፣ኢሕአዴግ ውስጥ ተሃድሶ መቷል፣ኢሕአዴግ አብዛኛው ወይንም 90 በመቶ የለውጥ ጉዞ ውስጥ ገብቶ የገባነውን ቃል ለመተግበርና ሕዝባችንን ይቅርታ ጠይቀን መካስ አለብን ብሎ ያምናል”ሲሉ ተናግረዋል።
“እዚህ ውስጥ ያልገባ ሃይል ካለ በሒደት እየለየን እናጠራለን፣በለውጥ ባቡር ውስጥ ያልገባ ኢሕአዴግ ሆኖ አይቀጥልም፣በለውጥ ባቡር ውስጥ ገብቶ የኢትዮጵያን ሕዝብ ፍላጎት የማያረጋግጥ ማንም ይሁን ማን ኢሕአዴግ ሆኖ አይቀጥልም”ሲሉ አጽንኦት ሰጥተዋል።
“የጀመርነውን ለውጥ ወደ ኋላ የሚቀለብስ ማንኛውንም ነገር ለመሸከም ዝግጁ አይደለንም ”በማለት አሳይታ ላይ ባደረጉት ንግግር አረጋግጠዋል።
“የኢትዮጵያን ሕልውና አደጋ ውስጥ የሚያስገባ፣ ሰላም የሚያሳጣን፣መልሶ ጭንቀት ውስጥ የሚያስገባን፣እናቶች ልጆቻቸው ወተው እስኪገቡ ድረስ የሚጨነቁባት ኢትዮጵያ ዳግም እንዳትመለስ መከፈል የሚገባው ዋጋ ይከፈላል፣ጠርተን፣ጠንክረን እንወጣለን ብለን ተስፋ እናደርጋለን”ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።