ለውጥን በሚፈልጉ ኃይሎችና ለውጥ በሚያደናቅፉ ኃይሎች መሃከል የሚደረገው ፍትጊያ መቀጠሉን ምሁራን ተናገሩ

ለውጥን በሚፈልጉ ኃይሎችና ለውጥ በሚያደናቅፉ ኃይሎች መሃከል የሚደረገው ፍትጊያ መቀጠሉን ምሁራን ተናገሩ
(ኢሳት ዜና ሰኔ 22 ቀን 2010 ዓ/ም) በመላው ኢትዮጵያ ላለፉት ሦስት ዓመታት የተከሰተውን ሕዝባዊ እንቢተኝነት ተከትሎ የሕዝቡን ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት በሚፈልጉት በጠቅላይ ሚንስትር አብይ አህመድ የሚመሩት የለውጥ ኃይሎችና የነበረውን የአፈና ስርዓት ለማስቀጠል በሚፈልጉ ኃይሎች መሃከል የሚደረገው ፍትጊያ መቀጠሉን ምሁራን ገለጹ።
በአሁኑ ወቅት በመላው ኢትዮጵያ ያለውን እንቅስቃሴ አስመልክቶ በአንቦ ዩንቨርሲቲ የወሊሶ ካንፓስ መምህርና ጦማሪ ስዩም ተሾመ እንዳሉት ”በአጠቃላይ በአገሪቱ ያለው ሁኔታ የለውጥ ሂደት ነው። መብት፣ ነጻነት፣ እኩልነት፣ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት እንዲገነባ የሚጠይቁ ዜጎች በመስቀል ዓደባባይ በመገኘት የለውጡ ኃይሎች አሳይተዋል። ያንን የለውጥ እንቅስቃሴ ማደናቀፍና የነበረውን ስርዓት ለማስቀጠል የሚሹ ወገኖች አሉ።
ፍርሃትንም ለማንገስ ዜጎች እንዳይተማመኑ ማድረግ፣ ዜጎችን መለያየት፣ እርስበርስ እንዳይተማመኑ በማድረግ አካላዊ ጉዳቶችን ማድረስ ዓላማቸው ነው። በአጠቃላይ በአገሪቱ በአሁኑ ወቅት ያለው ሁኔታ በለውጥ ሃይሎችና በጸረ-ለውጥ ሃይሎች መሃከል ፍርሃትና ነጻነት አንዱ ጎልቶ ለመውጣት የሚታገሉበት ሁኔታ ነው ያለው።” ብለዋል።
በመላው አገሪቱ የነበረውን የአፈና አገዛዝ በማንሳት የነጻነት፣ ዴሞክራሲና የእኩልነት ስርዓትን እንዲገነባ የሚደመረገውን ጥረት ለማደናቀፍ ፀረ-ለውጥ ኃይሎች ፍርሃትን መሳሪያ አድርገው የሚንቀሳቀሱ ኃይሎች ዜጎችን በቋንቋና በብሄር ለመለየት የሚያደርጉትን ጥረቶች ሕዝቡ በአንድነት እንዲታገልም ምሁሩ ጥሪ አድርገዋል።
”ፍርሃት በማንገስ፣ የዜጎችን ለመለያየት የሚያደርጉት ባለፈው 26 ዓመታት ያነገሱትን የአንድ ወገን ተጠቃሚነትና የበላይነት ለማስቀጠል ነው። ያንን የበላይነት ለማስቀጠል አለመረጋጋት እንዲሰፍን ያደርጋሉ። ያንን ለማስቀጠል የሚፈልግ ወገኖን እኩልነትን አይፈልጉም። ያንድን ወገን የበላየትን ለማስፈን የሚፈልግ የብዙሃንን እኩልነት ስለማይቀበል የህልውና ጥያቄ ነው የተፈጠረው። ፍርሃትን በማስፈን የነበረውን ማስቀጠል ስለሚፈልጉ መልሱ አለመፍራት ነው። የሚታገሉት የራሳቸውን ጥቅም ለማስጠበቅ ስለሆነ ሕዝቡ ከፍርሃት ቆፈንን በመውጣት መታገል አለበት።
ሕዝቡ በአንድነት ሆኖ ለውጡን ደግፎ የሚያስፈራሩትንና መጠቀሚያ የሚያደርጉትን በጋራ በመሆን ሕልውናውን ለማረጋገጥ በአንድነትን በመቆም በመተባበር ህልውናውን ለማስከበር ይቅርታን፣ ፍቅርን፣ ነጻነትን በዓደባባይ መስበክ መቻል አለበት። ይህ ሲሆን እነዚህ ወገኖች ይሸነፋሉ። በመንግስት በኩል የለውጡን እንቅስቃሴ ለማደናቀፍ የሚሞክሩት ሃይሎች ላይ ሕጋዊ እርምጃ በመውሰድ በሕግ ተጠያቂ ማድረግ አስፈላጊ ነው።” ሲሉ መምህርና ጦማሪ ስዩም ተሾመ አሳስበዋል።