(ኢሳት ዲሲ–ታህሳስ 30/2010)
የመከላከያ ሰራዊቱን በተመለከተ የሚነሱ ተቃውሞዎችን ተከትሎ ለኦሮሞና ለአማራ ተወላጆች የጄኔራልነት ማዕረግ ለመስጠት መወሰኑን ምንጮች ለኢሳት ገለጹ።
ማዕረጉ ይሰጣቸዋል የተባሉት መኮንኖች ለተሃድሶ ስልጠና መግባታቸው ተመልክቷል።
የኢሳት ምንጮች እንደገለጹት በመከላከያ ሰራዊቱ አመራር ውስጥ ያለውን ውጥረት በመቃወም የሚደረጉ ግፊቶችን ተከትሎ የአመራር ቦታዎቹን ከማስተካከል ይልቅ አዳዲስ ግለሰቦችን ከሌላ ብሔረሰብ ለመሾም ዝግጅት መጠናቀቁን መረዳት ተችሏል።
ከ30 የማያንሱ ሰዎች ይሾሙበታል በተባለው በዚህ ፕሮግራም ከ30 የማይናሱ ኮለኔሎች የብርጋዴር ጄኔራልነት ማዕረግ ያገኛሉም ተብሏል።
ተሿሚዎቹ በአብዛኛው ከኦሮሞና አማራ ብሔር እንደሚሆኑ የተገለጸ ሲሆን ከደቡብና ከትግራይ በተወሰነ ቁጥር ተሿሚዎቹ ውስጥ እንደሚካተቱም ምንጮች ገልጸዋል።
የኢሕአዴግ አጋር ፓርቲ የሚባሉት ከሚያስተዳድሯቸው ክልሎች ውስጥ የሚካተቱ መኖራቸውም ታውቋል።
አንዳንዶቹ ኮለኔል የሚባለው የማዕረግ እርከን ላይ ሳይደርሱ ሹመቱ ሊሰጣቸው ዝግጅቱ ተጠናቋል።
በዚህ የማዕረግ አሰጣጥ ቀደም ሲል የብርጋዴር ጄኔራልነት ማዕረግ ካገኙት ውስጥ የሜጀር ጄኔራልነትና የሌተናል ጄኔራልነት ማዕረግ የሚሰጣቸው መኖሩም ተገልጿል።
የኦሮሞና የአማራ ተወላጆች በዚህም ከፍተኛ ድርሻ እንደሚኖራቸው ተመልክቷል።
ቀን ያልተቆረጠለትና ነገር ግን በቅርቡ ይሰጣል የተባለውን ማዕረግ ተከትሎ ማዕረጉ ከሚሰጣቸው ውስጥ ከፊሉ የተሀድሶ ስልጠና መጀመራቸውን መረዳት ተችሏል።
የሹመት ስነስርአቱ በይፋ የሚገለጸው ከፕሬዝዳንቱ ጽህፈት ቤት በመሆኑ በአሁኑ ወቅት በኩባ ሃቫና የሚገኙት ፕሬዝዳንት ሙላቱ ተሾመ እንደተመለሱ ማዕረጉ ይሰጣል ተብሎ ይጠበቃል።
በአሁኑ ወቅት በሀገሪቱ መከላከያ ሰራዊት ውስጥ ያሉት ጄኔራሎች በመቶዎች የሚቆጠሩ በመሆናቸው ጥቂት የማይባሉት ተገቢ ቦታ ሳያገኙ በሕወሃት የጦር አዛዦች ስር ምክትል የሚባል ደረጃ እየተሰጣቸው በአብዛኛው ያለስራ መቀመጣቸውን የመከላከያ ምንጮች ይገጻሉ።
በሕዝባዊ ወያኔ ሀርነት ትግራይ መሪዎች ቀደም ሲል በአነስተኛ ቁጥርም ቢሆን በመከላከያ ሰራዊቱ ውስጥ የነበሩት የኦሮሞና የአማራ ተወላጆች አፈንጋጭ ሆነው ተገኝተዋል በሚል ደካማ የሚባሉ ሰዎችን ከአማራና ኦሮሞ እየፈለጉ ወደ ጄኔራል መኮንንነት እያስጠጉ ነው በሚል ተቃውሞዎች ሲቀርቡ ቆይተዋል።’
የሕዝባዊ ወያኔ ሃርነት ትግራይ የፖለቲካ አመራር ባሳለፈው ውሳኔ ከምርጫ 1997 ወዲህ የአየር ሃይል አዛዡን ሜጀር ጄኔራል አለምሸት ደገፌን ጨምሮ 10 ያህል የኦሮሞና የአማራ ጂኔራሎች ከሰራዊቱ መባረራቸውን ማስታወስ ተችሏል።
ብርጋዴር ጄኔራል ተፈራ ማሞና ብርጋዴር ጄኔራል አሳምነው ጽጌ መንግስትን ለመገልበጥ ሞክራችኋል በሚል በወህኒ ቤት ይገኛሉ።
ከተባራሪዎቹና ከታሳሪዎቹ ውስጥ የቀሩት ቀደምት ጄኔራሎች ሌተናል ጄኔራል ባጫ ደበሌና ሌተናል ጂኔራል አበባው ታደሰ በጡረታ ተወግደዋል።
ከሀገሪቱ እዞች ከትግራይ ተወላጆች ውጭ ተይዞ የነበረውን የምዕራብ ዕዝ ይመሩ የነበሩት ሌተናል ጄኔራል ብርሃኑ ጁላ ለሰላም ማስከበር ተልዕኮ ሲሔዱ ይህም ስፍራ ለትግራይ ተወላጅ በመሰጠቱ በሃገሪቱ ሁሉም ወታደራዊ እዞች እንዲሁም ልዩ ልዩ መምሪያዎች በትግራይ ተወላጆች መያዛቸውን የመከላከያ ምንጮች ይገልጻሉ።
ለሁለት አመታት በሀገሪቱ የቀጠለውን ተቃውሞ ተከትሎ ስብሰባ የተቀመጠው የኢሕአዴግ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ስብሰባ ላይ ከተነሱት ጉዳዮች አንዱ የሀገሪቱ የመከላከያ ሰራዊት አመራር ሙሉ በሙሉ በትግራይ ተወላጆች መያዙን የተመለከተ መሆኑንም መረዳት ተችሏል።