ኢሳት (መጋቢት 26 ፥ 2008)
በጅቡቲ ወደብ ለኢትዮጵያ የምግብ ተረጂዎች ሊደርስ የታሰበን የእርዳታ ዕህልን እንደያዙ ለቀናት ወረፋን ሲጠባበቁ የነበሩ መርከቦችን የጫኑትን የእርዳታ እህል ለማውረድ (ለማራገፍ) ወደ ጎረቤት ሶማሊላንድ በርበራ ወደብ አቀኑ።
አለም አቀፍ የእርዳታ ድርጅቶች በበኩላቸው ለተረጂዎች ሊደርስ የነበረው ድጋፍ በመዘግየቱ ምክንያት ድርቁ የሚያደርሰው ጉዳት እየከፋ መምጣቱን በድጋሚ ገልጿል።
የመንግስት ባለስልጣናት የጅቡቲ ወደብ ከአቅሙ በላይ በመጨናነቁ ሳቢያ ለተረጂዎች የእርዳታ እህልንና ማዳበሪያን የጫኑ መርከቦች ወደ ሱዳንና በርበራ ወደቦች እንዲያቀኑ ውሳኔ መሰጠቱን ለሃገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን ገልጸዋል።
የትራንስፖርት ሚኒስቴር ሃገሪቱ ከፍተኛ የሎጂስቲክ ችግር እንዳጋጠማትና ተሽከርካሪዎችን ለሱዳን ለመከራየት ድርድር እየተካሄደ መሆኑን ባለፈው ሳምንት ይፋ ማድረጉ ይታወሳል።
ችግሩ ከሁለት ሳምንት በኋላም እልባት ሊያገኝ ባለመቻሉ መንግስት የሱዳንና የበርበራን ወደቦች ለመጠቀም ውሳኔ ማስተላለፉን የፌዴራል ትራንስፖርት ባለስልጣን ዋና ስራ አስኪያጅ የሆኑት አቶ ካሳሁን ሃይለማሪያም ለመገናኛ ብዙሃን አስረድተዋል።
በጅቡቲ ወደብ ለአንድ ወር ያህል ወረፋን ሲጠባበቁ የቆዩት መርከቦች መኖራቸውንም ሃላፊው ያረጋገጡ ሲሆን፣ ድርጊቱ ለኢትዮጵያ ተጨማሪ ወጪን እንደሚያመጣም ተነግሯል።
በአሁኑ ወቅት ከ 10 የሚበልጡ መርከቦች የእርዳታ እህልንና ማዳበሪያን እንደያዙ በጅቡቲ ወደብ ወረፋን እየተጠባበቁ የሚገኙ ሲሆን፣ የተወሰኑት መርከቦች ደግሞ ወደሱዳንና በርበራ ወደቦች በማቅናት ላይ መሆናቸውን ታውቋል።
አለም አቀፍ የኣርዳታ ተቋማት በበኩላቸው የእርዳታ አቅርቦቱ ለተረጂዎች በመዘግየቱ ምክንያት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ለከፋ ችግር ተጋልጠው እንደሚገኙ በድጋሚ ገልጸዋል።
የእርዳታ አቅርቦት በመዘግየቱም ድርቁን ለመቅረፍ በሚደረገው ጥረት ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ እንደሚያሳድር የገለጹት ድርጅቶቹ ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት አፋጠኝ ርብርብን እንደሚያደርጉ ጠይቀዋል። በወደብ ከተፈጠረው መጨናነቅ በተጨማሪ የእርዳታ እህልን በሃገር ውስጥ ለማጓጓዝ የተሽከርካሪ እጥረት መፈጠሩን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በመግለጽ ላይ ነው።