ጥር ፴ (ሠላሳ)ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በቁጥር ብአዴን/ማዕ.ኮ/2131ሪ በቀን 23/05/2009 ዓ/ም ለኢህአዴግ ማእከላዊ ኮሚቴ ጽ/ቤት እንዲደርስ የተጠቃለለው የጥልቅ ትሃድሶ የመምህራን መድረክ ማጠቃላያ ሪፓርት ኢሳት እጅ ገብቷል፡፡ ይህ በኢሜል የተላከው ሰነድ እንደሚያሳያው ከ8 ሺ በላይ መምህራን በዞን ደረጃ ቀጠና ተለይቶ ውይይት አድርገዋል፡፡
በአምስት ዋና ዋና ምድቦች አርዕሰተ ጉዳዮች እየተመራ የተካሄደ ሲሆን ኢህአዴግ አደጋ ውስጥ መግባቱን የሚያስገነዝብ ነው፡፡ መምህራን ስለድህነት፣ ትምህርት ጥራት መጓደል ፣ በአገሪቱ ስለሚታየው የብሄረሰቦች ግጭት፣ ስለአንድ ብሄር የበላይነት፣ ስለ ጥላቻ፣ በአገሪቱ ስለሚታዩ ህዝባዊ ተቃውሞዎችና ስለኢህአዴግ ወቅታዊ ሁኔታ በርካታ አስተያየቶችን ሰጥተዋል።
“ኢህአዴግ በቅቶታል፣ የትግራይ የበላይነት አለ፣ የአማራ ክልል በልማት እየተጎዳ ነው፣ ዘረኝነት ተስፋፍቷል፣ ትምህርት ሞቷል፣ በአጠቃላይ አገዛዙ አገሪቱን መግዛት ባለመቻሉ በአስቸኳይ ስልጣኑን ይልቀቅ” የሚሉ አስተያየቶች ቀርበዋል።
በክልሉ የሚገኙ መምህራን የሰጡዋቸውን አስተያየቶች እና ለኢህአዴግ ማእከላዊ ኮሚቴ የተላከውን ሪፖርት ሙሉ ይዘት በልዩ ዝግጅት እንደምናቀርብ ለመግልጽ እንወዳለን።