ኢሳት (ጥር 3 ፥ 2008)
በኢትዮጵያ እየተባባሰ የመጣውን የድርቅ አደጋ ተከትሎ ለአስቸኳይ ጊዜ የምግብ እርዳታ ለተጋለጡ ሰዎች የሚያስፈልጋቸው የእርዳታ መጠን ከ760 ሺ ሜትሪክ ቶን በላይ መድረሱን መንግስት ማክሰኞ ባቀረበው የእርዳታ ጥያቄ አስታወቀ።
አለም አቀፍ የእርዳታ ተቋማት በበኩላቸው ለምግብ እርዳታ የተጋለጡ ሰዎች በቀጣዮቹ ሶስት ወራቶች ውስጥ ድጋፍ ካልጀመሩ ችግሩ የከፋ እንደሚሆን በድጋሚ አሳስበዋል።
ከ10 ሚሊዮን በላይ ለሚሆኑ ተረጂዎች የእርዳታ ጥሪን ያቀረቡ የመንግስት ባለስልጣናት የተወሰኑ ተቋማት ወደ 140ሺ ሜትሪክ ቶን እርዳታን ወደሃገር ውስጥ ለማስገባት እቅድ መያዛቸውንና የተቀረው ድጋፍ በመንግስት ለመሸፈን አስገዳጅ ሁኔታ መፈጠሩን ገልጸዋል።
ከተያዘው የፈረንጆች አዲስ አመት ጀምሮ የተረጂዎች ቁጥር ወደ 15 ሚሊዮን ሊደርስ እንደሚችል የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አስታውቋል።
የተረጂዎች ቁጥር በማሻቀብ ላይ በመሆኑም መንግስት ዓለም አቅፍ ለጋሽ ተቋማት ተጨማሪ ድጋፍን ማድረግ እንደሚገባቸው በእርዳታ ጥሪው አሳስቧል።
በአፋርና በሶማሊ ክልል በድርቁ የተጎዱ አካባቢዎች ወደረሃብ ደረጃ እየተሸጋገሩ እንደሚገኙ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ሰኞ ይፋ ማድረጉ የሚታወስ ሲሆን ይህንንም ተከትሎ የኢትዮጵያ መንግስት ማክሰኞ አዲስ የእርዳታ ጥሪን እንዳቀረበ ከሃገር ቤት የተገኘ መረጃ አመልክቷል።
የበጋ ወቅት እየተጠናከረ በመምጣቱም በድርቅ አደጋ የተጎዱ አካባቢዎች ከፍተኛ የውሃ እጥረት አጋጥሟቸው የሚገኝ ሲሆን እስካሁን ድረስም ወደ አንድ ሚሊዮን የሚጠጋ የቤት እንስሳት በድርቁ ሳቢያ መሞታቸው ተገልጿል።
በሃገሪቱ ታሪክ በ 50 አመት ወስት ሲከሰት የከፋው ነው የተባለው የዘንድሮው ድርቅ አደጋ እስከቀጣዩ አመት ሚያዚያ ወር ድረስ ቀጣይ መሆኑንም የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አመልክቷል።
በሺዎች ለሚቆጠሩ ትምህርት ትምህርት ቤቶች መዘጋት ምክንያት የሆነውን የድርቅ አደጋ ለመከላከል ከአንድ ቢሊዮን ዶላር በላይ የሚገመት የእርዳታ አቅርቦት እንደሚያስፈልግም ታዉቋል።
ከ180 በላይ ወረዳዎች ውስጥ የሚገኙ ከ10 ሚሊዮን በላይ ድጋፍ ፈላጊዎች የአስቸኳይ የምግብ እርዳታን እየተጠባበቁ እንደሚገኝ የእርዳታ ድርጅቶች ይገልጻሉ።