ኢሳት (መስከረም 10 ፥ 2009)
በኢትዮጵያ ለአስቸኳይ ጊዜ ለምግብ እርዳታ ከተጋለጡ በሚሊዮን ለሚቆጠሩ ሰዎች በመስከረም ወር መቅረብ የነበረበት የጥራጥሬና ቅባት እህሎች መቋረጡን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ማክሰኞ አስታወቁ።
በስድስት ክልሎች 9.7 ሚሊዮን የሚሆኑ ተረጂዎች አሁንም ድረስ የእርዳታ አቅርቦትን በመጠባበቅ ላይ ቢሆኑም ድጋፉ በተያዘው መስከረም ወር በአቅርቦት እጥረት ምክንያት መስተጓጎሉን ድርጅቱ ገልጿል።
ሃገሪቱ አጋጥሟት ያለውን ይህንኑ የጥራጥሬና ቅባት እህሎች አቅርቦት በቀጣዮቹ ሶስትና አራት ወራት ውስጥ ለሟሟላት የ131 ሚሊዮን ዶላር የገንዘብ ጉድለት አጋጥሞት መገኘቱን የአለም ምግብ ፕሮግራምም ዋቢ በማድረግ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ይፋ አድርጓል።
ከአለም አቀፍ ማህበረሰብ መገኘት የነበረበት ድጋፍ በተፈለገው መጠን ሊቀርብ ባለመቻሉ ምክንያት ለተረጂዎች መድረስ ያለበት መጠን እየቀነሰ መምጣቱም ታውቋል።
ከእርዳታ አቅርቦት ማነስ በተጨማሪ በአማራና ኦሮሚያ ክልሎች በመካሄድ ላይ ያሉ ህዝባዊ ተቃውሞዎችና አድማዎች በእርዳታ አቅርቦቱ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ማሳደሩን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አስታውቋል።
ከዚሁ ተቃውሞ ጋር በተገናኘ በሁለቱ ክልሎች የአስቸኳይ ጊዜ የምግብ ድጋፍ ማግኘት የነበረባቸው የ 51 ወረዳዎች በነሃሴ ወር ምንም እርዳታ ሳይቀርብላቸው መቅረቱን ድርጅቱ በድርቁ ዙሪያ ካወጣው ሪፖርት ለመረዳት ተችሏል።
ከ51 ወረዳዎች መካከል 17 የሚሆኑት ለሁለት ዙሪ ምንም አይነት የምግብ አቅርቦት እንዳላገኙ ያወሳው ድርጅቱ፣ የአማራና ኦሮሞያ ክልሎች በምግብ ድጋፍ አቅርቦት ልዩ ትኩረት ሊሰጣቸው እንደሚገባ አሳስቧል።
ከአንድ አመት በፊት በስድስት ክልሎች የተከሰተውን የድርቅ አደጋ እስከ ቀጣዩ አመት ድረስ ሊቀጥል ይችላል የሚል ስጋትን አሳድሮ የሚገኝ ሲሆን በአጠቃላይ ወደ 10 ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች ድጋፍ የሚፈልጉ እንደሆነ ታውቋል።