ሐምሌ ፲፯(አስራ ሰባት)ቀን ፳፻፭ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ባለፈው አመት የወር ደሞዛችን በአመት ከፍለናል አሁን ግን ዳግመኛ ለመከፈል አቅሙ ስሌለለን እና እየተባባሰ የመጣውን የኑሮ ውድነት ለመቋቋም ስለማንችል፣ ከእንግዲህ ወዲህ ገንዘብ ልንከፈል የምንችለው ባገኘንበት ጊዜ ብቻ ነው ” በማለት በአማራ ክልል የሚገኙ የመምህራን ማህበራት አስታውቀዋል፡፡
መንግስት ከሐምሌ ወር ጀምሮ ከሰራተኛው ለመቁረጥ አቅዶት የነበረ ቢሆንም ፣ በክልል ቢሮዎች ብቻ ከግማሽ በላይ የሚሆኑት የመንግስት ሰራተኛች ” የተሰጠን ቦንድ ይወሰድ እና ነጸ እንሁን ፤ 10 ፐርሰንት ብቻ ይቆረጥብን ፤ በልቼ ማደር ስላልቻልኩ ለሚቀጥለው ዓመት ይተላለፍልኝ” የሚሉ እጅግ በርካታ ደብዳቤዎች ለፍትህ ቢሮ ፤ ለሰራተኛ እና ማህበራዊ ጉዳይ በግልባጭ እንዲያቀውቁዋቸው ተደርገው በሰራተኞች ቀርበዋል፡፡
የተወሰኑት ሰራተኞች ደግሞ ” የልጆቻችንን መሰረታዊ ፍላጎቶች ማሟላት ስላቃተን እና የትምህርት ክፍያ ስለበረታብን ለብአዴን መዋጮ የሚቆረጥብን እንዲቆም እንጠይቃለን” የሚሉ ጥያቄዎችን አቅርበዋል።
የመንግስት አመራሮችም ” ያልተቸገረ የለም፣ ችግሩን ችላችሁ ገንዘብ እንዲቆረጥ ተስማሙ” በማለት ሰራተኛውን ለማሳመን ጥረት እያደረጉ ነው፡፡
አቶ ሀይለማርያም ደሳለኝ በቅርቡ ህዝቡ ግድቡን ለማስፈጸም የሚያበረከትው ድርሻ ትንሽ መሆኑንና አብዛኛው በመንግስት ወጪ የሚሰራ መሆኑን ተናግረዋል። ይሁን እንጃ ሟቹ ጠቅላይ ሚኒሰትር የግድቡን እቅድ ይፋ ሲያደርጉ፣ ግዱ ሙሉ በሙሉ በኢትዮጵያውያን ድጋፍ ይሰራል ማለታቸው ይታወቃል።