ለተፈናቃዮች የእርዳታ እህል ማቅረብ አልተቻለም ተባለ

(ኢሳት ዲሲ–ታህሳስ 2/2011) በቤንሻንጉል ጉምዝና አዋሳኝ የኦሮሚያ ክልል አካባቢዎች ባለው የጸጥታ ችግር ምክንያት ለተፈናቃዮች የእርዳታ እህል ማቅረብ አለመቻሉን የብሔራዊ የአደጋና ስራ አመራር ኮሚሽን አስታወቀ።

ፋይል

በሌላ በኩል በአካባቢዎቹ ለወራት የዘለቀውን ግጭት ለማስቆምና ታጣቂዎችን መሳሪያ ለማስፈታት የፌደራል መንግስት ተጨማሪ የመከላከያ ሰራዊት ማስገባቱ ታውቋል።

የብሔራዊ የአደጋና ስራ አመራር ኮሚሽን እንዳስታወቀው በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ባለው የጸጥታ ስጋት ምክንያት ለተረጂዎች እርዳታ ለማጓጓዝ የሄዱ ተሽከርካሪዎች ለአንድ ወር ያህል እንዲቆዩ ተደርገዋል።

            ለተረጅዎች ዕርዳታ ለማድረስ የሄዱት 5 ከባድ ተሽከርካሪዎች መመለስ ያልቻሉት በአካባቢው የሚንቀሳቀሱ ሃይሎች ጥቃት እየፈጸሙ በመሆናቸው ነው ተብሏል።

በአሁኑ ጊዜ በ10 ተሽከርካሪዎች የምግብ ዕርዳታ ተጭኖ ያለ ቢሆንም በጸጥታ ስጋት ምክንያት ወደ ስፍራው መንቀሳቀስ እንዳልቻሉ የኮሚሽኑ ባለስልጣናት ገልጸዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለም የፌደራል መንግስት በሁለቱ ክልሎች ያለውን ቀውስ ለማስቆም ተጨማሪ የመከላከያ ሰራዊቱን መላኩን ተገልጿል።