ለተለያዩ ጉዳዮች ወደ ኢትዮጵያ የሚጓዙ ሰዎች ቁጥር እየቀነሰ ነው ተባለ

ኢሳት (ህዳር 7 ፥ 2009)

በቅርቡ ተግባራዊ የተደርገውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ተከትሎ ለተለያዩ ጉዳዮች ወደ ኢትዮጵያ የሚጓዙ ሰዎች ቁጥር መቀነስ ማሳየቱን ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው አካላት ገለጹ።

የአዋጁ መውጣት በተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ላይ ስጋትን እንዳሳደረ የሚናገሩት እነዚሁ አካላት በተለይ ከአሜሪካ እንዲሁም ከአውሮፓ ሃገራት ወደ ሃገር ቤት የሚመጡ ሰዎች ቁጥር ካለፉት ጥቂት ወራት ወዲህ መቀነስ ማስመዝገቡን አስረድተዋል።

በሃገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ሲካሄድ የቆየው ህዝባዊ ተቃውሞና ባለፈው ወር ተግባራዊ የተደረገው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለቁጥሩ መቀነስ ምክንያት መሆኑን ለመረዳት ተችሏል።

በአዲስ አበባ እንዲሁም በክልል ከተሞች የሚገኙ የሆቴል አገልግሎት መስጫ ተቋማት በቱሪስቶችና በእንግዶች ቁጥር መቀነስ ሳቢያ ገቢያቸው እየቀነሰ መምጣቱን ይገልጻሉ።

ባለፈው ሳምንት ስድስት የስሎቫኪያ አራት የቼክ ሪፐብሊክ ቱሪስቶች በደቡብ ክልል በታጠቁ ሰዎች ዝርፊያ ተፈጽሞባቸው ሹፌራቸው መገደሉ የሚታወስ ነው። ይኸው ድርጊት ወደ ኢትዮጵያ ሊጓዙ በሚፈልጉ ቱሪስቶች ላይ ስጋት ማሳደሩን አስጎብኚ ድርጅቶች አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ቱሪዝም ድርጅት በበኩሉ በተያዘው በጀት አመት ሃገሪቱ ከቱሪስት ገቢ ታገኘዋለች ተብሎ የሚጠበቀው የውጭ ምንዛሪ ቅናሽን እንደሚያሳይ ገልጿል።

ባለፉት ሶስት ወራቶች ብቻ ዘርፉ የሰባት ሚሊዮን ዶላር (የ150 ሚሊዮን ብር) ጉድለት ማስመዝገቡ ይፋ ተደርጓል።