ለብዙ ዓመታት  ከኖሩበት ቀየ  መፈናቀላቸውን አርሶ አደሮች ተናገሩ

ግንቦት ፳፭(ሃያ አምስት)ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-በኦሮምያ ክልል በምእራብ ሸዋ ዞን በዳኖ ወረዳ አጂላ ዳሌ ቀበሌ ይኖሩ የነበሩ አርሶ አደሮች ለኢሳት እንደገለጹት ከ19 ዓመታት በላይ ከኖሩበት ቀየ በተለያዩ ሰበቦች ሀብትና ንብረታቸውን ተቀምተው ለቀው እንዲወጡ በመደረጋቸው  ቤት አልባ ሆነው ለችግር ተዳርገዋል።

“መንግስት በአካባቢው እንድንኖር ፈቃድ ሰጥቶን የሚፈለግብንን ግብር እየከፈልን አካባቢውን ስናለማ ነበር” የሚሉት አርሶ አደሮች፣ ሀብትና ንብረት ካፈራን በሁዋላ ” የያዛችሁት መሬት ለቤተክርስቲያን ማሰሪያ ይፈለጋል” በሚል ሰበብ ምንም ተለዋጭ ቦታ ሳይሰጠን በፍርድ ቤት እንድንለቅ ተደርገናል ብለዋል።

“ጉዳዩን ለሚመለከታቸው የወረዳ ባለስልጣናት ቢያመለክቱም፣ የወረዳ አስተዳዳሪ የሆኑት አቶ ለገሰ ንጉሴ  ከሳሽ ሆነው በመቅረባቸው ምንም መፍትሄ ሊያገኙ አለመቻላቸውን አርሶደአሮች አክለው ገልጸዋል።

ጌታቸው ገዴ፣ ዘውዱ ገብረመድህን፣ ቦጋለ ተካ፣ ወ/ሮ ጌጤ ሃይሌ፣ ዳኜ ይልማ፣ ቄስ ልኬ አወቀ፣ አበራ ካሳ፣ ቄስ ተካ ጸጋው፣ ሃብታሙ ክብረት እና ደብረ ደነቀ የተባሉትና ሌሎችም ተፈናቅለዋል።

በጉዳዩ ዙሪያ የወረዳውን አስተዳዳሪ አቶ ለገሰ ንጉሴን ለማነጋገር በተደጋጋሚ ሙከራ ብናደርግም አልተሰካልንም።