ኢሳት (መጋቢት 12 ፥ 2008)
የኢትዮጵያ መንግስት ላለፉት አስር አመታት ያህል ከሃገር ውስጥና ከውጭ ባለሃብቶች ለሰፋፊ የእርሻ መሬቶች ሲሰጥ የቆየውን ፈቃድ እንዲቀር አደረገ።
የግብርና ኢንቨስትመንት እና የመሬት አስተዳደር ኤጀንሲ ከዘርፉ ይመጣል ተብሎ የታሰበው የቴክኖሎጂ ሽግግር የተፈለገውን ውጤት ሊያመጣ ባለመቻሉ ምክንያት ፕሮግራሙ እንዲቆም መደረጉን ገልጿል።
ኤጀንሲው ባለፉት ጥቂት አመታት ከአራት ክልሎች 470 ሺህ ሄክታር መሬትን ተረክቦ ለ131 ባለሃብቶች ቢሰጥም ውጤታማ የሆኑት ከ30 በመቶ እንደማይበልጡም ይፋ አድርጓል።
በቅርቡ በጋምቤላ ክልል አንድ መሬት ለበርካታ ባለሃብቶች እየተሰጠ ባለሃብቶቹ ከልማት ባንክ በርካታ ሚሊዮን ብርን በመበደር በመንግስት ላይ ኪሳራ ማምጣታቸው ይታወሳል።
B.H.O. የተሰኘ አንድ የህንድ ኩባንያ ከጋምቤላ ክልል 27ሺ ሄክታር መሬት ተረክቦ ከልማት ባንክ ከ89 ሚሊዮን ብር በላይ ብድር ተፈቅዶለት በስድስት አመታት ውስጥ 3ሺ ሄክታር በማይሞላ መሬት ላይ ብቻ ስራ ጀምሮ ከነብድሩ መጥፋቱን የኤጀንሲው ባለስልጣናት ለመገናኛ ብዙሃን አስታውቀዋል።
ባለፈው አመት ብቻ 43 ሰፋፊ የእርሻ መሬቶች ተደራርበው በተለያዩ ባለሃብቶች መሰጠታቸውን የኤጀንሲው የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ አቶ ዳንዔል ዘነበ ገልጸዋል።
በተለያዩ ክልሎች ለሃገር ውስጥና ለውጭ ባለሃብቶች ሲሰጡ የነበሩ ሰፋፊ የእርሻ መሬቶች በመንግስት ላይ ከፈጠሩት ችግር በተጨማሪ በነዋሪዎች ዘንድ ተቃውሞ ሲቀርብባቸው መቆየቱም ይታወሳል።
የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽ/ቤትም በጋምቤላ በደቡብ እና በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች ለባለሃብቶች በሚሰጡ መሬታችን ላይ ተፈጥሯል በተባለው ችግር ዙሪያ ጥናት እንዲካሄድ መወሰኑም ታውቋል።
የሰፋፊ እርሻ መሬቶች መሰጠት መቆምን ተከትሎም የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ለዘርፉ የሚሰጠውን ብድር ያቋረጠ ሲሆን፣ ባንኩ ለሰፋፊ እርሻዎች የሰጠው ብድር በትክክል የት እንደደረሰ እንደማይታወቅ የባንኩ ፕሬዚደንት አቶ ኢሳያስ ባህረ ለሃገር ውስጥ ጋዜጦች ይፋ አድርገዋል።
ባለፉት አምስት አመታት ብቻ ባንኩ ለሰፋፊ የእርሻ መሪተ ባለሃብቶች 6 ቢሊዮን ማበድሩ ታውቋል።
ይሁንና፣ ባንኩ ከአምስት አመት በፊት ጀምሮ በአጠቃላይ ምን ያህል ገንዘብ ለባለሃብቶች እንዳበደረ የታወቀ ነገር የሌለ ሲሆን በሂደቱም መንግስት በቢልዮን የሚቆጠር ገንዘብ የት እንደገባ እንዳማያውቅ ባለስልጣናት አረጋግጠዋል።