የህወሃት/ኢህአዴግ መንግስት የኢትዮጵያ ህዝብ ባላወቀውና ባልወሰነበት ሁኔታ ለሱዳን መሬት ለመስጠት መንቀሳቀሱ በእጅጉ እንዳበሳጫቸው ኢትዮጵያውያን ገልጸዋል።
“እንዲህ አይነት መንግስት አይቼ አላውቅም፣ መንግስት ሊባል አይችልም፣ በአገር ላይ የሚሰሩት ስራ ሁሉ እጅግ የሚያሳዝን ነው፣ የኢትዮጵያ ወገን አይደሉም” በማለት አስተያየት የሰጡት አንድ የሰሜን ጎንደር ነዋሪ፤ ስርዓቱን ተባብረን እስካልገታነው ድረስ መዋረዳችን ይቀጥላል ብለዋል።
ሌላው አስተያየት ሰጪ ደግሞ “ በኢትዮጵያ ‘አፈሮቿ ባህር ተሻግረው እንዳይሄዱ የወራሪዎቿን እግር አራግፋችሁ ላኩ’የሚሉ የአገር መሪዎች ነበሩ፣ የኢትዮጵያ መሬት በደምና ባጥንት ተጠብቆ የቆየ ነው። አሁን በስልጣን ላይ ያሉት ግለሰቦች መሬቱዋን ቆርሰው ሲሰጡ ህሊናቸውን አይሰቀጥጣቸውም፣ ለታሪካቸውም አይጨነቁም “ ብለዋል። የአገሪቱን አንድነት የመጠበቅ ሃላፊነት የወጣቱ በመሆኑ፣ ወጣቱ ለራሱና ለመጪው ትውልድ ሲል ድርጊቱን ይቃወም ብለዋል።
የሱዳን አርሶአደሮች ከኢትዮጵያ ተቆርሶ የሚሰጣቸው መሬት በቂ አይደለም በሚል አቤቱታ አቅርበዋል። የገዳሪፍ አስተዳዳሪ በበኩላቸው ለአገራቸው የሚመለሰው መሬት የዲፕሎማሲ ድል መሆኑን ተናግረዋል።
የሱዳን አርሶአደሮች ከ60 ስኩየር ኪሎሜትር በላይ መሬት እንደማይሰጣቸው ገልጸዋል። ሊመለስልን ይገባል የሚሉት የመሬት ስፋት ግን 500 ሺ ስኩየር ኪሎሜትር ነው።
በኢትዮጵያ በኩል ዜናው በሚስጢር መያዙ ያበሳጫቸው አንድ አስተያየት ሰጪ በበኩላቸው፣ የባድመን ጉዳይ በማስታወስ መረጃውን ዛሬ በሚስጢር ቢይዙት ነገ ይፋ መሆኑ አይቀርም፤ እውነታውን ከኢትዮጵያ ህዝብ ለመደበቅ ለምን እንደተፈለገ አይገባኝም፣ ፓርላማ ቢኖረን፣ በጉዳዩ ዙሪያ ጥያቄ አቅርቦ እንዲመለስ ማስደረግ ይችል ነበር። ሁሉም ነገር ድፍን ያለ ነው” ሲሉ መናገራቸውን ወኪላችን ገልጿል።