ለሰአታት የተቋረጠው አለም አቀፍ በረራ ዘግይቶ ጀመረ

(ኢሳት ዲሲ–ሚያዚያ 9/2010) የኢትዮጵያ ሲቪል አቭዬሽን የአየር ትራፊክ ሰራተኞች በመቱት አድማ ለሰአታት የተቋረጠው አለም አቀፍ በረራ ዘግይቶ ጀመረ።

ወደ ሶስት ሰአታት የተስተጓጎለው በረራ መነሻው ምክንያት የአየር ትራፊክ ሰራተኞች ለባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ያቀረቡት ጥያቄ ምላሽ ባለማግኘቱ እንደሆነም ተመልክቷል።

በውጤቱም 48 በረራዎች ተስተጓጉለዋል፣ወደ ለንደንና ዱባይ የሚበሩ አውሮፕላኖችም ከዘገዩት ውስጥ ይጠቀሳሉ።

በኢትዮጵያ ሰአት አቆጣጠር ከጠዋቱ 3 ሰአት እስከ 4.30 የተስተጓጎለው በረራ የቀጠለው ጥያቄውን ያነሱትን ሰራተኞች በማንሳት በሌሎች በመተካት እንደሆነም የኢትዮጵያ ሲቪል አቬሽን ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ገልጸዋል።

ዋና ዳይሬክተሩ ኮለኔል ወሰንየለህ ሁነኛው እንደተናገሩት ሰራተኞቹ ቅሬታቸውን ስራቸውን እያከናወኑ ማቅረብ ሲገባቸው ይህንን ባለመፈጸማቸው ከሃላፊነት መነሳታቸውን ገልጸዋል።

የበረራ ትራፊክ መቆጣጠሪያ ሰራተኞች ተቃውሞ ማሰማት የጀመሩት ከትላንት ሰኞ ጀምሮ መሆኑ የተገለጸ ሲሆን ምላሽ ሲያጡ ዛሬ ማለዳ ስራ አቁመዋል።

የሲቪል አቬሽን ባለስልጣን ሃላፊዎች እንደሚገልጹት ተቃውሞው ከበአል ቀናት ክፍያ ጋር የተያያዘ  እንዲሁም የኢትዮጵያ ሲቪል አቬሽን ባለስልጣን ሶስት ፈረቃ የነበረውን ስምሪት ወደ ሁለት ዝቅ ማድረጉ እና  ደሞዝና መዋቅራዊ ማስተካከያዎች በሰራተኞቹ ዘንድ መነሳታቸውን ከዘገባዎቹ መረዳት ተችሏል።ሆኖም በሰራተኞች በኩል የተሰጠ መግለጫ የለም።

ዛሬ በአየር ትራፊክ ሰራተኞቹ አድማ ቦሌ የሚያርፉና ከቦሌ የሚወጡ 48 በረራዎች መዘግየታቸውን አለም አቀፍ የበረራ ጠቋሚ ተቋማት አስታውቀዋል።ከዘገዩት አለም አቀፍ በረራዎች ውስጥ ወደ ኬንያ ናይሮቢ፣ወደ ዩናይትድ አረብ ኤምሬት ዱባይ፣ወደ ካርቱም ሱዳን፣ወደ ብሪታኒያ ለንደን የሚበሩ አውሮፕላኖች እንደሚገኙበትም ለማወቅ ተችሏል።

በየቀኑ 250 ያህል በረራዎች ያስተናግዳል በሚባለው ቦሌ አለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ለ48 በረራዎች መስተጓጎል ምክንያት የሆነው አድማ ሰራተኞቹን በሌላ በመተካት ፍጻሜ ማግኘቱን የሲቪል አቬሽን ሃላፊዎች ለመንግስታዊ መገናኛ ብዙሃን ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን ወደ ኬንያ ናይሮቢ ሲጓዙ ከነበሩ መንገደኞች አንዱ የነበረው የቢቢሲ ጋዜጠኛ ኢማኑኤል ኢጉንዛ በተፈጠረው ሁኔታ በረራው ሁለት ሰአት ዘግይቶ ናይሮቢ መድረሱን በቲውተር ገጹ ላይ አስፍሯል።