ኢሳት ዜና (መስከረም 19 ፣ 2008)
የተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ መብት ኮሚሽን በጄኔቭ ስዊዘርላንድ እየተካሄደ ካለው 30ኛ ጉባኤ ጋር ተያይዞ በተጠራ መድረክ ላይ የተጋበዙት የኢትዮጵያ መንግስት ልዑካን ስብሰባ ረግጠው ወጡ።
ስኞ እለት የኢትዮጵያን ሰብዓዊ መብት በተመለከተ በተጠራው ስብሰባ ላይ የተገኙትና በኋላ በቀረበው ሪፖርት ሳይደሰቱ ስብሰባውን ረግጠው የወጡት የኢትዮጵያ መንግስት ልዑካን ወደ ስብሰባው አልተመለሱም።
የኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ተወካዮች ጨምሮ የተለያዩ አለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶችና ግለሰቦች በጄኔቭ ስዊዘርላንድ በመገኘት በወቅታዊ የኢትዮጵያ የሰብኣዊ መብት አያያዞች ዙሪያ መወያየታቸውን እማኞች አስታውቀዋል።
ይሁንና የኢትዮጵያ መንግስት ተወካዮች በመድረኩ ሊነሱ በሚችሉ የሰብዓዊ መብት ጉዳዮች ዙሪያ ምላሽና ማብራሪያ ይሰጣሉ ተብሎ ሲጠበቅ፣ ከጉባኤው ረግጠው መውጣታቸው ታውቋል።
ሂውማን ራይትስ ዎችን ጨምሮ በርካታ አለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች በኢትዮጵያ ያለው የሰብዓዊ መብት ረገጣና አፈና ተባብሶ መቀጠሉን ገልፀዋል።
ሁሉንም የፓርላማ ወንበሮች በብቸኝነት ተቆጣጥሮ የሚገኘው ገዢው የኢህአዴግ መንግስት፣ የዜጎችን ሃሳብን የመግለጽ መብት ከማስፋፋቱ በተጨማሪ በነጻ የመገናኛ ብዙሃን ላይ የሚወስደው እርምጃ አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን ድርጅቱ አመልክቷል።
ከትናንት በስቲያ ሰኞ የተካሄደውን የሰብዓዊ መብት መድረክ ያዘጋጀው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብኣዊ መብት ኮሚሽን በተለያዩ ጊዜያት በኢትዮጵያ ስላለው የሰብኣዊ መብት አያያዝ ስጋቶችን ሲገልፅ መቆየቱ ይታወሳል።
በጄኔብ በተካሄደው በዚሁ ልዩ መድረክ የተሳተፉ በርካታ ድርጅቶች በኢትዮጵያ ወቅታዊ የሰብዓዊ መብት አያያዝ ዙሪያ ረፖርት ማቅረባቸውንም በመድረኩ የተሳተፉ አካላት ገልፅዋል።
የእንግሊዝ የፓርላማ አባላትን ጨምሮ በርካታ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጀቶች ኮሚሽኑ የአቶ አንዳርጋቸው ጽጌ አያያዝን ጨምሮ በተለያዩ የፖለቲካ እስረኞች ላይ ክትትልን እንዲያደርግ ጥያቄ አቅርበው እንደሚገኙም ተችሏል።
የኢትዮጵያ መንግስት ተወካዮች መድረኩን ረግጠው ስለወጡበት ምክንያት የሰጡት ምላሽ የለም።