መስከረም ፲ (አስር) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ለከተማ ቤቶች መስሪያ፣ ለልማት ወይም ህገወጥ ግንባታ በሚል አርሶ አደሮች ያለምንም ክፍያ ከይዞታ መሬታቸው እየተፈናቀሉ ማህበራዊ ቀውስ እየተፈጠረ መሆኑን ከተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የሚደርሱን መረጃዎች ያመለክታሉ።
በኦሮምያ ክልል በ አዳማ ከተማ በ10 ሺዎች የሚቆጠሩ አርሶ አደሮችና ነዋሪዎች ቦታቸውን እንዲለቁ ማስጠንቀቂያ የደረሳቸው ሲሆን፣ በርካታ ቤቶችም ፈርሰዋል።
በማሳ ያለው ሰብል ሲደርስ መሬቱን ለመቀማት ዝግጅት ላይ መሆናቸውን ነዋሪዎች ተናግረዋል። ቅዳሜ ከፍተኛ ህዝብ በተገኘበት ስብሰባ ቢደረግም፣ ምክትል ከንቲባው በአቤቱታ አቅራቢዎች ላይ ” ብትፈልጉ ውጭ ማደር ትችላላችሁ ” በማለት ተሳልቀዋል።
በሰሜን ሸዋ በጫጫ ወረዳ ደግሞ አጅማ ወንዝን ለመገደብ በሚል ሰበብ ከነብር ዋሻ እስከ አሞራ ገደል ባሉት አካባቢዎች የሚገኙ በብዙ መቶዎች የሚቆጠሩ አርሰዶአሮች እንዲነሱ ትእዛዝ ተላልፎላቸዋል። አርሶ አደሮቹ ” ሆን ተብሎ እኛን ለመበታታን የታቀደ ነው” በማለት የመንግስትን ድርጊት አጥብቀው ተቃውመዋል።
ለሸንኮራ ልማት በሚል በተለያዩ ክልሎች የሚፈናቀሉ አርሰዶአሮች ለኢሳት የድረሱልን ጥሪዎችን ቢያሰሙም ፣ እስካሁን መፍትሄ የሚሰጥ አካል ሊገኝ አልቻለም። ተስፋ የቆረጡ አርሶደሮች እና ቤቶቻቸው በህገወጥ መንገድ የፈረሰባቸው ወደ ከተሞችና ወደ ውጭ አገራት እየተሰደዱ መሆኑን መረጃዎች ያሳያሉ።