ጥር ፳፮ (ሃያ ስድስት)ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በአዲስ አበባ መስተዳድር የጉለሌ እጽዋት ማእከል በሚል ሲጠራ የነበረውና በቅርቡ የመለስ ዜናዊ ፓርክ ተብሎ የተሰየመው እንጦጦ ላይ ከፍተኛ ወጪ ወጥቶበት የታጠረው ጥብቅ የደን ተቋም በያዝነው አመት 200 ሚሊዮን ብር የሚጠጋ ወጪ ሂሳብ ፣ ለኦዲት ምቹ ያልሆነ ነው በሚል ባክኖ መቅረቱን ምንጮች ገልጸዋል።
ለፓርኩ ዝግጅት የወጣ ወጪ ቢኖርም አብዛኛው ወጪ ህጋዊ ደረሰኝ ባልቀረበበት ሁኔታ የወጣ በመሆኑ እንደባከነ ገንዘብ ተቆጥሯል። ምንጮች እንዳሉት ከፍተኛ ሙስና በተፈጸመበት በዚህ ፕሮጀክት ማንም ደፍሮ የጠየቀ አካል የለም።
በቀድሞው ጠ/ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ስም የተለያዩ ፕሮጀክቶች የተነደፉ ቢሆንም፣ ሁሉም ከፍተኛ ሙስና ተፈጽሞባቸዋል። በመለስ ዜናዊ ስም የሚካሄዱ ፕሮጀክቶች በሙሉ በወ/ሮ አዜብ መስፍን የበላይ ክትትል የሚካሄዱ ናቸው።
በሌላ በኩል በመከላከያ ሰራዊት ውስጥ የሚታየው የበጀት ጉድለት እየሰፋ መምጣቱን የኢሳተ ምንጮች ገልጸዋል። ኦዲት እንዳይደረግባቸው ትእዛዝ ከተላለፈባቸው ግዢዎች ውጭ ባለው በጀት ወታደራዊ አዛዦች ከፍተኛ ዝርፊያ እያካሄዱ ነው። ከእቃዎች ግዢ ጀምሮ ለነዳድጃና አበል በሚወጣው ወጪ ላይ ከፍተኛ ምዝበራ መፈጸሙ፣በሰራዊቱ ቀለብ እና የሎጂስቲክስ አቅርቦት ላይ ከፍተኛ ጫና እየፈጠረ ነው፤፡ ሰራዊቱ በበቂ ሁኔታ ቀለብ፣አልባሳትና ጫማዎችን ለማግኘት እየተቸገረ መሆኑን የሚገልጹት ምንጮች፣ በአንጻሩ ጥቂት አዛዦች በሰራዊቱ ስም የሚወጣውን በጀት በሰበብ አስባቡ ይዘርፋሉ ብለዋል።
ከጦር መሳሪያ ግዢ ጋር በተያያዘ የሚፈጸመውን ሙስና መቆጣጠር እንደማይቻል የሚገልጹት ምንጮች፣ ህጋዊ ኦዲተር በሚቆጣጠረው በጀት ይህን ያክል ሙስና ከተፈጸመ፣ ኦዲተር በማይቆጣጠረውንና አብዛኛውን የመከላከያ በጀት በሚሸፍነው ምን ያክል ሙስና ሊፈጸም እንደሚችል መገመት አያቅትም ሲሉ ምንጮች አስተያየታቸውን ይሰጣሉ።