ኢሳት (የካቲት 21 ፥ 2009)
በቀጣዩ አመት በኢትዮጵያ ሊካሄድ ለታቀደው የህዝብና ቤቶች ቆጠራ ከተመደበው ሶስት ቢሊዮን ብር መካከል አንድ ቢሊዮን ብር ለ180ሺ ዘመናዊ ዲጂታል ታብሌቶች (የእጅ ኮምፒውተሮች) መግዣ ተመደበ።
ለቆጠራው ከሚያስፈልገው ገንዘብ ውስጥ አብዛኛው በአለም አቀፍ ተቋማት ድጋፍ የሚሸፍን መሆኑን የማዕከላዊ ስታቲስቲክስ ኤጀንሲ ሃላፊዎች መግለጻቸውን አዲስ ፎርቹን የተሰኘ የቢዝነስ ጋዜጣ ዘግቧል።
ኤጀንሲው የዘመናዊ ኮምፒውተሮቹን በአንድ ቢሊዮን ብር ለመግዛት ባወጣው ጨረታ የቻይናው ZTE እና Huawei ኩባንያዎች ጨምሮ ዘጠኝ ድርጅቶች ኮምፒውተሮቹን ለማቅረብ ፍላጎት ማሳየታቸው ታውቋል።
ለዚሁ የሰዎችና ቤቶች ቆጠራ ወደ 150 ሺ አካባቢ ባለሙያዎች እንዲሰማሩ የገለጸው የማዕከላዊ ስታቲስቲክስ ኤጀንሲ የሚገዛው የኮምፒውተር ቁጥር በምን ምክንያት ከባለሙያው ቁጥር ሊበልጥ እንደቻለ የሰጠው መረጃ የለም።
ከቆጠራው በኋላ በአንድ ቢሊዮን ብር የሚገዙት ኮምፒውተሮች ምን ጥቅም ላይ እንደሚውሉ የተጠየቁት የኤጀንሲው ተጠባባቂ ሃላፊ የሆኑት አቶ አሳልፈው አበራ፣ ኮምፒውተሮቹ መረጃዎን ለማሰባሰብ ለተመሳሳይ አላማ ይውላሉ ሲሉ ምላሽን ሰጥተዋል።
ከ10 አመት በኋላ የሚካሄደው ይኸው ብሄራዊ የህዝብና ቤቶች ቆጠራ በቀጣዩ አመት ህዳር ወር እንደሚካሄድ የሚጠበቅ ሲሆን፣ 180ሺ ዲጂታል ኮምፒውተሮች የፌታችን ሃምሌ ወር ወደ ሃገር ይገባሉ ተብሏል።
በቀጣዩ አመት በሚካሄደው በዚሁ ቆጠራ የኢትዮጵያ አጠቃላይ ህዝብ ቁጥር ወደ 94 ሚሊዮን አካባቢ ይደርሳል ተብሎ እንደሚጠበቅም የማዕከላዊ ስታቲስቲክስ ኤጀንሲ አመልክቷል።
ይሁንና የአለም ባንክ የኢትዮጵያ ህዝብ ቁጥር እንደፈረጆቹ አቆጣጠር 2015 አም 99.3 ሚሊዮን አካባቢ መድረሱን በድረ-ገጹ ላይ በመረጃነት አስቀምጧል።