ለሁለት ቀናት የተጠራው የአዲስ አበባ ታክሲ አሽከርካሪዎች አድማ ወደ ኦሮምያ ተዛመተ

የካቲት ፳፪ (ሃያ ሁለት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በአዲስ አበባ ለሁለት ቀናት የተጠራው የታክሲ አሽከርካሪዎች አድማ ለሁለተኛ ቀን ከቀጠለ በሁዋላ፣ ከሰዓት በሁዋላ በተለይም ከቀኑ 10 ሰአት ጀምሮ ታክሲዎች ቀስ በቀስ ስራ ጀምረዋል።በአዲስአበባ የተደረገውን አድማ ተከትሎ፣በኦሮምያ የተለያዩ ከተሞችም ተመሳሳይ የስራ ማቆም አድማ ተደርጓል።በሆለታ፣ ቡራዩ፣ግንጪ፣ አምቦ፣ ወሊሶና አካባቢዋ የትራንስፖርት አገልግሎት ተቋርጦ ውሎአል።
በአዲስ አበባ ጠዋት አካባቢ ጥቂት ታክሲዎች ስራ ለመጀመር ቢወጡም፣ህዝቡ በአብዛኛውን ከቤቱ ባለመውጣቱ፣ ለወትሮው ይታይ የነበረው ግርግር፣ እስከ ምሳ ሰአት ድረስ በነበረው ጊዜ አልታየም።በርካታ ተማሪዎች አድማውን ተከትሎ ወደ ትምህርት ቤት አለመሄዳቸው ታውቋል።
ትራፊክ ፖሊሶች ከሰአት በሁዋላ ስራ የጀመሩትን ታክሲዎች በማስቆም ፣የአሽከርካሪዎችን መንጃ ፈቃድ ሲጠይቁ ታይተዋል።
መንግስት አዲስ የወጣውን የትራፊክ ደንብ ለሶስት ወራት ማራዘሙን ቢያስታውቅም፣ የአድማው አስተባባሪዎች በበኩላቸው ደንቡ ሙሉ በሙሉ እንዲሰረዝላቸው ይጠይቃሉ።