ለሀገር ነጻነት የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንደሚያደርጉ የቀድሞ የሀገር መከላከያና ፖሊስ ሰራዊት ማህበር ስራ አስፈጻሚ አባላት ገለጹ

(ኢሳት ዜና–ነሐሴ 29/2009) ወጣቱ ትውልድ ለሀገር ነጻነት የሚያደርገውን ትግል በመደገፍ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንደሚያደርጉ የቀድሞ የሀገር መከላከያና ፖሊስ ሰራዊት ማህበር ስራ አስፈጻሚ አባላት ገለጹ።

ማህበሩ 3ኛ አመታዊ በአሉን ባለፈው ቅዳሜ በአትላንታ ማካሄዱን በተመለከተ የስራ አስፈጻሚ አባላቱ ሻለቃ ደምሴ ዮሐንስና ሻለቃ ሱራፌል ዘውዴ ለኢሳት እንደገለጹት የቀድሞ ሰራዊት አባላት አሁን ባለው አገዛዝ ቢበተንም አሁንም ለሀገሩ ያለው ፍቅር ያልተነካ ነው።

እናም ዛሬም ነገም አሁን ላለውም ሆነ ለሚመጣው ትውልድ ያሉንን ወታደራዊ እሴቶች እናስተላልፋለን ብለዋል።

የቀድሞ የመከላከያና የፖሊስ ሰራዊት ማህበር አመራር አባላት ሕዝቡ ለነጻነቱ የሚያደርገውን መስዋእትነትና ዘርፈ ብዙ ትግል ለድል እስኪበቃ ድረስ አጋር መሆናቸውን በ3ኛ አመት ክብረ በአላቸው አረጋግጠዋል።

የስራ አስፈጻሚ አባሉ ሻለቃ ደምሴ ዮሐንስ እንደገለጹት የቀድሞ ሰራዊት አባላት በአሁኑ ጊዜ የሚደረገውን ትግል በመደገፍ በተለይ ለወጠቱ ትውልድ ወታደራዊ እሴቶችን ለማስተላለፍ ማህበሩ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል።

የማህበሩ ሌላው ስራ አስፈጻሚ ሻለቃ ሱራፌል ዘውዴ በበኩላቸው ሕዝቡ ለሰራዊቱ ያለውን ድጋፍና ፍቅር አድንቀዋል።

እናም የሕዝቡ ድጋፍ እኛም ለሀገራችን ያለንን ጽኑ ፍቅር እንድናጠናክር አድርጎናል ነው ያሉት።

በቀድሞ የመከላከያና የፖሊስ ሰራዊት ማህበር 3ኛ አመታዊ ክብረ በአል ላይ የማህበሩ ሊቀመንበር የነበሩት ሻለቃ ደምሴ ዮሀንስና የማህበሩ ዋና ጸሀፊ ሻለቃ አበበ ይመኑ የ3 አመታት የስራ አፈጻጸማቸውን ለታዳሚዎች ገልጸዋል።

በበአሉ ላይ ሜጀር ጄኔራል መርዳሳ ሌሊሳ የእንኳን አደረሰን መልእክት በስልክ አስተላልፈዋል።

የሜጀር ጄኔራል መርእድ ንጉሴና ብርጋዴር ጄኔራል አዲስ አግላቸው ቤተሰቦችም በስነስርአቱ ላይ ታድመዋል።

በክብር እንግድነትም አርቲስት አለምጸሐይ ወዳጆ፣ጋዜጠኛ ርዕዮት አለሙና ወጣቱ ፖለቲከኛ ሐብታሙ አያሌውም ተገኝተዋል።–የአጋርነት መልእክታቸውንም አስተላልፈዋል።

የቀድሞው የመከላከያና የፖሊስ ሰራዊት ማህበር ሶስተኛ አመት በአልን አስመልክቶ ለኢትዮጵያ ሳተላይት ቴሌቪዥንና ሬዲዮ/ኢሳት/፣ለኢትዮጵያ ሚዲያ ፎረም፣ለአባይ ሚዲያ፣ለዲሲ ግብረሃይልና ለሌሎች ተቋማት እንዲሁም አስተዋጽኦ ላደረጉ ግለሰቦች የእውቅናና የምስጋና ሽልማት አበርክቶላቸዋል።