ኢሳት (ጥር 2 ፥ 2009)
አዲስ አበባ ከተማን ጨምሮ በተለያዩ የክልል ከተሞች ህገወጥ የውጭ ምንዛሪ ግብይት ይካሄድባቸዋል በተባሉ አካባቢዎች ዕርምጃን የሚወስድ ሃገር አቀፍ ኮሚቴ መቋቋሙ ተገለጸ።
ከአንድ ሳምንት በፊት በጠቅላይ ሚኒስቴር ጽ/ቤት ልዩ ትዕዛዝ የተቋቋመው ይኸው ኮሚቴ ሃገሪቱ ለከፋ የውጭ ምንዛሪ እጥረት እንድትዳረግ አስተዋጽዖ አድርገዋል በተባሉ አካላት ላይ ጥብቅ እርምጃን እንደሚወስድ ካፒታል የተሰኘ ሳምንታዊ የቢዝነስ ጋዜጣ ዘግቧል።
በተለምዶ “ጥቁር ገበያ” ተብሎ በሚጠራው የገንዘብ ልውውጥ ዙሪያ ጥናቱን ያካሄደው የፋይናንስ ደህንነት ማዕከል ቁጥሩ ከፍተኛ የሆነ የውጭ ምንዛሪ በህገወጥ መንገድ ከሃገሪቱ በመውጣት ላይ መሆኑን እንደተረጋገጠ ጋዜጣው የማዕከሉን ሃላፊዎች ዋቢ በማድረግ አስነብቧል።
ለተለያዩ ጉዳዮች ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡ የውጭ ሃገር ዜጎች እንዲሁም በውጭ ምንዛሪ ክፍያን የሚያገኙ ሰዎች ለህገወጥ የገንዘብ ልውውጥና ዝወውር አስተዋፅዖ ማድረጋቸውን የማዕከሉ ሃላፊ አቶ ገመቹ ወዮማ ገልጸዋል።
ሹፌሮች፣ ደላሎችና ሌሎች አካላት በዚሁ “ጥቁር ገበያ” ድርጊት ላይ ተሳታፊ መሆናቸውን የተናገሩት አቶ ገመቹ፣ አዲስ የተቋቋመው ልዩ ሃይል የሃገሪቱ የድንበር አካባቢዎችን ጨምሮ በተለያዩ ስፍራዎች ዕርምጃን እንደሚወስድ አስረድተዋል።
ሃገሪቱ አጋጥሟት ባለው የውጭ ምንዛሪ እጥረት ዙሪያ ሰኞ መግለጫን የሰጡ የመንግስት ሃላፊዎች የችግሩ መባባስን ተከትሎ ወዳጅ የተባሉ የባህረ ሰላጤ ሃገራት ገንዘባቸውን በኢትዮጵያ እንዲያስቀምጡ የማግባባት ስራ መጀመሩን ይፋ አድርገዋል።
ካለፉት ሶስት አመታት ወዲህ የኢትዮጵያ ውጪ ንግድ ገቢ እየቀነሰ መምጣቱ ለውጭ ምንዛሪ ክምችት እጥረት ዋነኛ ምክንያት መሆኑ ተነግሯል።
በመንግስት ባንኮችና በጥቁር ገበያ መካከል ያለው የዶላር ምንዛሪ ሰፊ ልዩነት እያሳየ በመምጣቱ ምክንያት በርካታ ሰዎች ወደ ጥቁር ገበያ በማቅናት ላይ መሆናቸው ተመልክቷል። የግል እና የመንግስት ባንኮች አንድ የአሚሪካን ዶላር በ22 ብር ከ35 ሳንቲም በመግዛት ላይ ሲሆኑ፣ በጥቁር ገበያ አንድ ዶላር 27 ብር አካባቢ እየተገዛ መሆኑም ታውቋል።
የምጣኔ ሃብት ባለሙያዎች በበኩላቸው መንግስት ከዚህ በፊት በጥቁር ገበያ ላይ የወሰደው ዕርምጃ የተፈለገውን ውጤት ሊያመጣ እንዳልቻለ አውስተው፣ መንግስት ችግሩን ለመቅረፍ የተሻለ የግዢ መጠን ተግባራዊ ማድረግ እንዳለበት አስረድተዋል።
የአለም ባንክ እንዲሁ ኢትዮጵያ ያጋጠማትን የውጭ ምንዛሪ እጥረት ለመቅረፍ እና የተሻለ የውጭ ኢንቨስትመንት ለመሳብ ብር ከዶላር ጋር ያለውን የምንዛሪ መጠን ከፍ ማድረግ እንዳለበት መጠየቁ ይታወሳል።
ይሁንና፣ መንግስት ዕርምጃውን ከጥቅሙ ጉዳቱ ይበልጣል በማለት በብር ላይ የማስተካከያ ዕርምጃ እንደማይወስድ በድጋሚ አስታውቋል።