ህዝባዊ ንቅናቄው በመላ ኢትዮጵያ ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚችል ተነገረ

ኢሳት (ነሃሴ 3 ፥ 2008)

በሳምንቱ መገባደጃ በኦሮሚያና በአማራ ክልሎች በተካሄዱ ህዝባዊ የተቃውሞ ሰልፎች ከ100 የሚበልጡ ሰዎች መንግስት የጸጥታ ሃይሎች መገደላቸውን ተከትሎ፣ ህዝባዊ ተቃውሞው በመላ ኢትዮጵያ ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚችል ተነገረ።

የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ አባል የሆኑት አቶ ሙላቱ ገመቹ አሜሪካ አገር ለሚተላለፈው ለኤንቢሲ (NBC) ለተባለው የቴሌቪዥን የዜና አውታር፣ “ሰዎች በመንግስት ላይ ተስፋ ቆርጠዋል፣ መንግስት ደግሞ የሰላማዊ ሰልፈኞችን ፍላጎት አላሟላም” በማለት ተናግረዋል።

ከዚህ በኋላ የሚደረግ ህዝባዊ ተቃውሞው ከቁጥጥር ውጭ ሊወጣ እንደሚችል አቶ ገመቹ ለዚሁ የቴለቪዥን ጣቢያ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ መንግስት በየቦታው የጦር ሃይልን አሰማርቶ ተማሪዎችንና ተቃዋሚ ፓርቲ ደጋፊዎችን ይገላል፣ ይደብድባል፣ ያስራል ያሉት አቶ ገመቹ፣ በመላው ኦሮሚያ የወጡት ሰላማዊ ሰልፈኞች በበኩላቸው በኢትዮጵያ ጸጥታ ሃይሎች የታሰሩ የፖለቲካ እስረኞችና ጋዜጠኞች እንዲፈቱና፣ የሁሉም ዜጎች የሰብዓዊ መብቶች እንዲከበሩ እየጠየቁ እንደሆነ አስረድተዋል።

የዋጋ ንረት እየከፋ፣ የመብራት፣ ውሃና፣ የመሰረተ ልማቶች አቅርቦቶች ጨርሰው የጠፉበት ሁኔታ ነው ያሉት አቶ ገመቹ፣ “የየዕለት ህይወት አስቸጋሪ ሆኗል፣ ህዝቡ ከዚህ በላይ ዝምታን ማስተናገድ አይችልም” ሲሉ ለቴሌቪዥን ጣቢያ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

በተመሳሳይ መልኩ አልጀዚራ አንድ ስማቸው ያልተገለጸን ዲፕሎማት ጠቅሶ በኦሮሚያና በአማራ ክልሎ ሰላማዊ ሰልፈኞች ላይ በመንግስት የተወሰደው ዘግናኝ ምላሽ ህዝቡን ለበለጠ ንዴትና ተቃውሞ ሊቀሰቅስ እንደሚችል ዘግቧል።

የአምነስቲ ኢንተርናሽናል የምስራቅ አፍሪካ ምክትል ዳይሬክተር የሆኑት ሚሼል ካጋሪ በበኩላቸው፣ የኢትዮጵያ መንግስት አመጹን ለማስቆም የተጠቀመው ስልታዊ የሃይል ምላሽ ስህተት እንደነበር ገልጸዋል።

በባህርዳር የተፈጸመው ግድያም “የጅምላ ፍጅት ነው ሊባል እንደሚችል የአምነስቲ ኢንተርናሽናል ምንጮችን ጠቅሶ አልጀዚራ ማክሰኞ ዘግቧል።