መስከረም ፲፩ (አሥራ አንድ) ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- 34 የትግራይ ተወላጆች ባወጡት መግለጫ ፣ “ህወሓት/ኢህአዴግ ተቋማዊ ባደረገው የዘውግ ፖለቲካ ምክንያት ህዝባችን ተከፋፍሎ ኢትዮጵያውያን በአገራቸው ውስጥ በተወሰኑ ክልሎች እንደ ባዕድ የሚታዩበት ሁኔታ “ እንዲከሰት አድርጓል ብለዋል።
“ህወሓት/ኢህአዴግ ስልጣኑን ፍፁማዊ ለማድረግ ሃይማኖትን በመሳሪያነት ስለሚጠቀም በክርስቲያኖች ውስጥና በሙስሊሞች ውስጥም ወደ ግጭት የሚያመራ ክፍፍል ፈጥሯል” የሚሉት የተለያዩ የተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅት መሪዎች፣ አክቲቪስቶችና ታዋቂ የጻፉት መግለጫ፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ስርዓቱን ለማቆየት የተገነባው የዘውግና የሃይማኖት ክፍፍል ስርዓቱን ለማስወገድ ወደሚጠቅም መሳሪያነት እየተቀየረ ብለዋል።
በአገራችን ያሉ ዋናዎቹ ችግሮች በማለት ከዘረዘሩዋቸው መካከል “ ህወሓት/ኢህአዴግ ገዳይ፣አፈኝና ከፋፋይ መሆኑና ህዝባችን በህይወት የመኖር ዋስትና ማጣቱ፣ ሰብአዊና ዴሞከራሲያዊ መብቶቹ መረገጣቸውና ባገሩ ውስጥ በነፃነት መኖር አለመቻሉ “ የሚሉትን ጠቅሰው፣ በኢህአዴግ ውስጥ ህወሓት ጉልበት በሚጠቀሙ ተቋሞች፡ በሰራዊቱ፣ በደህንነትና በእስር ቤቶች፣ በአስተሳሰብ ላይ ጫና በሚያደርጉ ተቋሞች፡ በመገናኛ ብዙሃንና በሃይማኖታዊ አመራሮች፣ በውጭ ጉዳይ ፣ ከፍተኛ ያገሪቱን ሃብት በመቆጣጠርና በመዝረፍ በዘውግ ላይ የተመሰረተ ቡድናዊ የበላይነት ይዟል ብለዋል።
እነዚህን ችግሮች ለማስወገድ ወሳኙ እርምጃ ህወሓት/ኢህአዴግ ከስልጣን አስወግዶ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት መገንባት ነው የሚለው መግለጫ፣ ህወሓት/ኢህአዴግ በህዝብ ላይ ከፍተኛ ጭፍጨፋ ሊያካሂድ እንደሚችል አስጠንቅቀዋል። አባይ ፀሃየና ስዩም መስፍን በትግራይ ህዝብ ላይ ያነጣጠረ እነሱ „የዘር“ የሚሉትና ከሆሎካውስትና ከሩዋንዳ እልቂት ጋር የሚያመሳስሉትና የእርስ በርስ ጦርነት አስከትሎ አገሪቷን የሚበታትን አደጋ እንደሚያሰጋ የሚገልፁት ማስፈራሪያ ፣ የእርስ በርስ ጦርነት ለመግታትና የኢትዮጵያ አንድነትን ለመጠበቅ እርምጃ የሚወስዱ አስመለስለው ተቃውሞ ያነሳባቸውን ህዝብ ለመጨፍጨፍ የሚጠቀሙበት የለመዱት ስልት ነው ሲል ያትታል።
አባይ ፀሃየና ስዩም መስፍን የትግራይን ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ መመስረት አላማቸው እንደሆነ በማኒፌስቶ ከገለፁት ጥቂት የህወሓት መስራቾች ውስጥ ስለሆኑ ለኢትዮጵያ አንድነት ተቆርቋሪዎች መስለው የመቅረብ የሞራል ብቃት የላቸውም የሚሉት የትግራይ ተወላጆች፣ ሰራዊቱና የመንግስት ታጣቂው ሃይል የህወሓት/ኢህአዴግ መሪዎች በወገኑ ላይ የጭፍጨፋ ወንጀል እንዳያስፈፅሙት መቃወም አለበት ብለዋል።
ህወሓት/ኢህአዴግ በሚወስዳቸው የጭካኔ እርምጃዎች ምክንያት በህዝብ ውስጥ ስጋት መስፈኑንም አልሸሸጉም። በዚህ የውጥረት ሁኔታ ስሜታቸውን መቆጣጠር የማይችሉና በህዝብ ውስጥ ግጭት የሚያስከተሉ እርምጃዎችን የሚወስዱ ግለሰቦችና ቡድኖች ሊያጋጥሙ ስለሚችሉ፣ ሁሉም ፍትህ፣ ሰላምና አንድነት የሚፈልጉ ወገኖች ለዘመናት አብሮ በኖረውና ነፃነቱን በጠበቀው ህዝብ ውስጥ ግብታዊ ግጭት እንዳይፈጠር ከፍተኛ ጥረት እንዲያደርጉ አሳስበዋል።
“ሌሎችም በዲያስፖራው የሚኖሩ የትግራይ ተወላጆች የትግራይ ህዝብ ከጥንትም ለወደፊትም እጣ ፈንታው ከሌላው የኢትዮጵያ ህዝብ ጋር መሆኑንና ጥቅሙና ህልውናው የሚጠበቀው በፍትህ፣ በዴሞክራሲ፣ በእኩልነትና በአንድነት ከሌላው የኢትዮጵያ ህዝብ ጋር ሲሆን ብቻ መሆኑን ተገንዝበው፤ የህወሓት ባለስልጣኖች በስልጣናቸው ላይ ለመቆየት የሚያደርጓቸውን መሰሪ ቅስቀሳዎች በማጋለጥና የሚፈፅሟቸውን ጭፍጨፋዎች በማውገዝ ድምፃቸውን እንዲያስሰሙና ወደ ትግሉ እንዲቀላቀሉ “ ጥሪያቸውን አቅርበዋል።