ነኅሴ ፳ (ሀያ) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ሟቹ ጠ/ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ያስቀመጡት የመተካካት ፖሊሲ በህወሃት ነባር አመራሮች ሲተች፣ ብአዴኖች ፖሊሲውን ሙሉ ለሙሉ ተግባራዊ ማድረግ ባለመቻላቸው ግራ ተጋብተዋል። የአቶ መለስ የመተካካት ፖሊሲ በ2007 ዓም ሁሉም የድርጅቱ ነባር አመራሮች በአዳዲስ ወጣት አመራሮች ይተካሉ የሚል ነበር። ይሁን እንጅ ህወሃት እያካሄደ ባለው መደበኛ ጉባኤ በአቶ መለስ ወቅት ከአመራር ቦታቸው የተነሱት ነባር ታጋዮች በጉባኤው እንደገና በመምረጥና በመመረጥ መብት እንዲሳተፉ ተደርጓል። ከህወሃት ስልጣን ተገለው የነበሩት አቶ ስብሃት ነጋ፣ ስዩም መስፍን፣ አርከበ እቁባይ፣ ብርሃነ ገብረከርስቶስና ሌሎች 17 የቀድሞ ታጋዮች በጉባኤው በታዛቢነት እንዲገኙ ቢጋበዙም፣ የጉባኤው አባላት ግለሰቦቹ በመተካካት ስም ተገፍተው ወጥተዋል ስለዚህም በሙሉ ስልጣን ይሳተፉ የሚል ጥያቄ በማቅረባቸው፣ ጉባኤው የመተካካቱን ፖሊሲ በመቀልበስ እንዲሳተፉ ወስኖላቸዋል።
የደህንነት ሹሙ ጌታቸው አሰፋ፣ የመተካካት ፖሊሲው ተቀናቃኞችን ለመግፋት ተብሎ የወጣ ነው ብለው መናገራቸውን የህወሃት አባላት እየገለጹ ሲሆን፣ ፖሊሲው እንከን የለበትም፣ በመተካካት ስም አንድም ሰው አልተገፋም፣ ተገፋሁ ያለ ሰው ካለ ይናገር በማለት ወ/ሮ አዜብ መስፍን ብቻ የቀድሞ ባለቤታቸውን ፖሊሲ ከትችት ለመከላከል ደፍረው አስተያየት ሰጥተዋል። ይሁን እንጅ አቶ ስዩም መስፍን ” እሳቸው ራሳቸው ሳያምኑበት ተገፍተው እንደወጡ” ንግግር ማድረጋቸውን የህወሃት ደጋፊዎች በማህበራዊ ድረገጾች ጽፈዋል።
አቶ ስዩም መስፍን ከሶስት አመት በፊት ለኢቲቪ እና ኤስቢስ ለተባለ የውጭ ሬዲዮ በሰጡት ቃለምልልስ ፣ እርሳቸውም ሆኑ ሌሎች አመራሮች የመተካካት ፖሊሰውን አምነውበት ስልጣናቸውን መልቀቃቸውን ተናግረው ነበር። ይሁን እንጅ ቃላቸውን አጥፈው፣ አሁን “ተገፍቼ ሳላምንበት ወጣሁ” ማለታቸው የሰውየውን ማንነት፣ የአገሪቱን መሪዎች ስብእናና አቶ መለስን ምን ያክል ይፈሩዋቸው እንደነበር አመላካች ነው የሚሉ አስተያየቶች እየቀረቡ ነው።
በተመሳሳይ መንገድ መተካካቱ ለ2 አመታት ሲመከርበት ቆይቶ ሁሉም የድርጅቱ መሪዎች ተስማምተውበት ተግባራዊ ማድረጋቸውን የገለጹት አቶ አርከበ እቁባይ፣ ከአምስት አመታት በሁዋላ የተናገሩትን አጥፈው እንደገና ተመልሰዋል።
ወትሮውንም በመተካካት ፖሊሲ ስም የሚደረገውን የማባረር ዘመቻ ሲቃወሙ የቆዩት አቶ ስብሃት ገብረእግዚአብሄር በጉባኤ ባለሙሉ መብት ሆነው መሳተፋቸው፣ ከመለስ ሞት በሁዋላ ሲያደርጉት ሲሰሩት የነበረው የፖለቲካ ስራ መሳካቱን የሚያሳይ ነው። ነባር አመራሮቹ ወደፊት መምጣታቸው የሃይል አሰላለፉን ይቀይረው አይቀይረው አልታወቀም ይሁን እንጅ ወ/ሮ አዜብ መስፍን ብቻ የመለስ ራእይ ተከራካሪ ሆነው መቅረባቸው ፣ የመለስን ራእይ እናስቀጥላለን በሚል ሲገባ የነበረው ቃል ወደ ጎን መባሉን እንዲሁም የመለስ ሌጋሴ እየተቀበረ መምጣቱን እንደሚያሳይ አስተያየቶች እየተሰነዘሩ ነው።
በህይወት ካሉት የብአዴን መስራቾች መካከል እስካሁን ድረስ ከድርጅቱ ጋር የተጓዙት አመራሮች፣ በጤናና በተለያዩ ሰበቦች ስልጣናቸውን የለቀቁ ሲሆን፣ ከድርጀቱ መስራቾች መካከል አቶ በረከት ስምኦን ብቻ በማእከላዊ ኮሚቴ አባልነት እንዲቀጥሉ ተወስኗል። አቶ በረከት ቀድም ብሎ በኢሳት እንደተዘገበው ከብአዴን የስራ አስፈጻሚነትና ከኢህአዴግ የምክር ቤት ስልጣናቸው ተነስተዋል። ይሁን እንጅ እንደ አቶ አዲሱ ለገሰ ወደ ተራ አባልነት ከመውረድ በማእከላዊ ኮሚቴ አባልነት መቆየትን መርጠዋል።
ኦህዴድ ቀድም ብሎ ያሰናበታቸውን እነ አባዱላ ገመዳን መልሶ ወደ ስልጣን አላመጣም። በስራ አስፈጻሚት የተመረጡት አብዛኞቹ ቀድም ብሎ በስልጣን ላይ የነበሩት ናቸው።
ብአዴንና ኦህዴድ ነባር አመራሮቻቸውን እየቀነሱ፣ ህወሃት ነባር አመራሮችን ወደ ስልጣን የሚያመጣበት አሰራር በኢህአዴግ ውስጥ ብዥታና አለመተማመን ሊፈጥር ይችላል ሲል ዘጋቢያችን አስተያየቱን አሰፍሯል።
ሪፖርተር ጋዜጣ ባወጣው ዘገባ ደግሞ በህወሃት ጉባኤ ላይ አንድ የሃይማኖት አባት ፣ የድርጅቱ መሪዎች ቀድሞ አንግተውት የነበረውን ዓላማ እንደረሱ፣ ፍትሕ በገንዘብ እየተገዛ የክልሉ ሕዝብ የማያውቀው አዲስ ባህል በመጎልበቱ ይህንንም እንደሚዋጉት መናገራቸውን ገልጿል። ‹‹እሳት ያልፈራ ሕዝብ እናንተን የሚፈራ ይመስላችኋል?›› ሲሉም ጥያቄ አቅርበዋል። ” መተካካት ወደ መገፋፋት በመቀየሩ ያለ ዕድሜና አቅም ማነስ ዶ/ር አርከበና አምባሳደር ብርሃነ እንዲወጡ መደረጉ እንዲሁም እንደ ድሮው መገማገምና አንዱ አንዱን ተጠያቂ ማድረግ በመሸፋፈንና በመጠባበቅ መቀየሩም በጉባኤው ላይ መነሳቱን ጋዜጣው ዘግቧል።