ህወሃት ዶ/ር መረራን ጨምሮ ሌሎች የፖለቲካ እስረኞችን በአስቸኳይ እንዲፈታ የኢትዮጵያ ሃገራዊ ንቅናቄ ጥሪ አቀረበ

ኢሳት (ታህሳስ 3 ፥ 2009)

የህዝባዊ ወያኔ ሃርነት ትግራይ (ህወሃት) መራሹ አገዛዝ ሃገርን ከጥፋት ለመታደግ ዶ/ር መረራ ጉዲናንም ሆነ ሌሎች የፖለቲካ እስረኞችን በአስቸኳይ እንዲፈታ የኢትዮጵያ ሃገራትዊ ንቅናቄ ጥሪ አቀረበ።

ንቅናቄው የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግሬስ (ኦፌኮ) ሊቀመንበር ዶ/ር መረራ ጉዲናን መታሰር አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ እንዳለው በኢትዮጵያ ያለው አገዛዝ የፖለቲካ ሜዳውን ክፍት በማድረግ ሁሉም ወገኖች የሚሳተፉበትን አገር አቀፍ ጉባዔ እንዲካሄድ ሁነታዎችን ማመቻቸት አለበት። merera-gudina

የኢትዮጵያ ሃገራዊ ንቅናቄ መግለጫ ላይ አንደተጠቀሰው በዶር መረራ ላይ የተወሰደው የእስር እርምጃ የሚያሳየው አገዛዙ ተስፋ መቁረጡንና ወደ ጥፋት የመሄድ አዝማሚያ ነው።

ዶ/ር መረራ ጉዲና በብዙዎቹ ዘንድ እንደሰላማዊ ትግል ተምሳሌን የሚቆጠሩ የፖለቲካ መሪ መሆናቸውን ንቅናቄው በመግለጫው ጠቅሷል።

አገዛዙ በእስር ቤት ያጎራቸውን የፍትህ፣ የነጻነትን፣ የዴሞክራሲያዊ የእኩልነት ጥያቄዎች ግንባር ቀድም አራማጆች ህልም እውን ለማድረግም ሁሉም ዜጋ እጅ ለእጅ ተያይዞ እንዲታገል የኢትዮጵያ ሃገራዊ ንቅናቄ ጥሪ አቅርቧል።

የህወሃት አገዛዝ ተወግዶ ፍትህ ዴሞክራሲና ነጻነት በኢትዮጵያ እንዲሰፍን የሚፈልግ ሁሉ በሃገራዊ ንቅናቄው የተጀመረውን ትግል በመቀላቀል ትግሉን እንዲደግም መግለጫው አሳስቧል።

ዓለም አቀፍ ማህበረሰብን ከጨቋኙ አገዛዝ ጋር ከመተባበር ይልቅ ከኢትዮጵያ ህዝብ ጎን እንዲቆሙም ንቅናቄው ጥሪ አቅርቧል። ሃገራዊ ንቅናቄው በኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ግንባር፣ በአርበኞች ግንቦት 7 በአፋር ህዝብ ፓርቲ በሲዳማ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ የተመሰረተ መሆኑ ይታወቃል።