ኢሳት (የካቲት 23 ፥ 2009)
የህወሃት/ኢህአዴግ አማጺያን ወደ አዲስ አበባ እየገፉ በመጡበት ወቅት የመንግስት መቀመጫ ከአዲስ አበባ ለማንሳትና ወደ ደቡብ ወይንም ምስራቅ ለመውሰድ ክርክር መደረጉን ተገለጸ። በቀድሞ የኢትዮጵያ መንግስትና በአማጺያን መካከል የተደረገው ድርድርም በአሜሪካ ጣልቃገብነት እንደከሸፈ ይፋ ሆኗል።
ይህ የተጋለጠው በለንደን በተካሄደው ድርድር የኢትዮጵያ መንግስት ልዑካን በመምራት በሂደቱ ተዋናይ በነበሩት በጠ/ሚኒስተር ተስፋዬ ዲንቃ መጽሃፍ ላይ ነው።
በዚህ ሳምንት ለንባብ የበቃውና የፊታችን ቅዳሜ በሚመረቀው የሟች ጠ/ሚ/ር ተስፋዬ ዲንቃ መጽሃፍ እንደተመለከተው፣ የለንደኑ ድርድር ሳይጀመር ነበር የተጨናገፈው።
ኮ/ል መንግስት ሃይለማሪያም ስልጣን ለቀው ከሃገር ከወጡ በኋላ ሁኔታዎች በመለዋወጣቸው የመንግስትን መቀመጫ ወደ አዋሳ ወይንም ድሬዳዋ ለመውሰድ የነበረው እቅድ ጄኔራል ተስፋዬ በመሩት ስብሰባ ላይ ውድቅ መደረጉም በሟቹ ጠ/ሚ/ር ተስፋዬ ዲንቃ መጽሃፍ ላይ ይፋ ሆኗል።
በቅርቡ ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩትና በለንደኑ ኮንፈረንስ የኢትዮጵያ መንግስት ልዑካን ቡድን የመሩት የቀድሞ ጠ/ሚ/ር አቶ ተስፋዬ ዲንቃ Ethiopia during the Derg years መጽሃፍ በሳምንቱ መጨረሻ በዋሽንግተን ዲሲ እንደሚመረቅም ይፋ ሆኗል። አሳታሚ ድርጅቱ ጸሃይ ፐብሊሸር እንዳስታወቀው የቀድሞ ጠ/ሚ/ር አቶ ተስፋዬ ዲንቃ Ethiopia During the Derg Years (ኢትዮጵያ በደርግ አመታት) በሚል ርዕስ የጻፉት መጽሃፍ የፊታችን ቅዳሜ የካቲት 25, 2009 በፈረንጆቹ አቆጣጠር March 4, 2017 በዋሽንግተን ዲሲ በጆርጅ ዋሽንግተን ዩኒቨርስቲ ለው ስኩል ይመረቃል።