ኢሳት (ነሃሴ 2 ፥ 2008)
በሰሜን ጎንደር አንዳንድ የሃይማኖት አባቶች ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ የአካባቢው ነዋሪዎች ጠየቁ።
ሰሞኑን ከወልቃይት የማንነት ጥያቄ ጋር ተያይዞ የተቀጣጠለውን ህዝባዊ እምቢተኝነት መንግስት ባሰማራቸው የመከላከያ፣ የፖሊስና ሌሎች የጸጥታ ሃይሎች አማካኝነት በቁጥጥር ስር ማዋል ስለተሳነው የሃይማኖት ተቋማትንና የሃይማኖት አባቶችን ተጠቅሞ ህዝባዊ ንቅናቄውን ለማጨናገፍ እየሰራ መሆኑን ድርጊቱን በቅርበት የሚከታተሉ የሰሜን ጎንደር ነዋሪዎች ለኢሳት ገለጹ።
እነዚህ በዳንሻ እና ሰሮቃ አካባቢ የሚኖሩ ነዋሪዎች እንደገለጡት ከሆነ፣ ከክልሉ የተነሱ ባለስልጣናት እና የአካባቢው ካድሬዎች የሃይማኖት አባቶችን በማስጠራት ህዝባዊ እምቢተኝነቱን እንዲያስቆሙ ተማጽነዋል። በተለይም የኢትዮጵያ ተዋህዶ ኦርቶዶክስ አባቶች በአካባቢው ከሚገኙት ደብሮች ታቦት ይዘው በመውጣት ህዝቡን እንዲለምኑ ትዕዛዝ መተላለፉን አሳውቀዋል።
በሃይማኖት ተቋማቱ ተሰግስገው የሚገኙና የስርዓቱ አገልጋዮች የሆኑ ጥቂት የሃይማኖት አባቶች የተሰጣቸውን የመንግስት ተልዕኮ ለማስፈጸም ቢሯሯጡም በብዙሃኑ ተቀባይነት ማግኘት እንዳልቻሉ ለኢሳት የአካባቢው ነዋሪዎች ገልጸዋል። ህዝቡም በተለያዩ መንግድ ከዚህ እኩይ ተግባራቸው እንዲቆጠቡ ይልቁንስ መስዋዕት እየሆነ ካለው ህዝባቸው ጎን በመሰለፍ ታሪካዊ ሃላፊነታቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል።
ይህን ማድረግ ከተሳናቸው ግን የህዝቡን ደም ከሚያፈሰው የህዝቡን ጥያቄ ከሚያፍነውና ህይወት ከሚቀጥፈው ስርዓት ለይቶ እንደማያያቸው አስጠንቅቋል።