የካቲት ፲፭ ( አሥራ አምስት )ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በህወሃት ኩባንያ ሙሉ ድጋፍ እና በኢትዮጵያ አየር መንገድ ትብብር ህወሃት የተመሰረተበትን 42ኛ አመት የልደት በአል በአለማችን እጅግ ዘመናዊና ውድ በሚባለው ቡርጂ አል አራብ ጁሚራህ ሆቴል ውስጥ ከአርብ እስከ እሁድ እንደሚያከብር የኢሳት ምንጮች ገልጸዋል።
በልዩ ትእዛዝ በተዘጋጁ አምስት አውሮፕላኖች የህወሃት መስራች አባላትና ባለስልጣኖች እንዲሁም ወጣት የህወሃት ደህንነቶች፣ ባለሃብቶችና ጠንካራ አባላት ከዛሬ ረቡዕ ጀምሮ ወደ ዱባይ በረራ ያደርጋሉ። እንግዶቹ ዘመናዊ በሚባሉት Abidos Hotel ፣ Apartment Dubailand፣ Saffron Boutique Hotel እና Fortune Karama Hotel መኝታ የተያዘላቸው ሲሆን፣ በቆይታቸው ሙሉ ወጪያቸው በድርጅታቸው ኩባንያ ይሸፈንላቸዋል።
ህወሃት ህዝብ በተራበበትና ከፍተኛ ችግር ላይ በወደቀበት በዚህ ወቅት በአሉን በውጭ አገር ለማክበር የመረጠው፣ ከህዝብ አይን ለመሸሽና ከትችት ለመዳን ሲባል መሆኑን ምንጮች ገልጸዋል።
በርካታ የህወሃት ባለስልጣናት ድርጅታቸው በአሉን በውጭ ለማክበር ማሰቡን በአድናቆት ተመልክተውታል። “ በያመቱ በአገር ውስጥ ከሚደረገው አሰልቺ በአል የተለየ ዝግጅት ማዘጋጀቱ፣ ለነጻነቱም ለምቾቱም ጥሩ ነው” ሲል አንድ ተጋባዥ እንግዳ አድናቆቱን ለኢሳት ዘጋቢ ገልጿል።
በአለማችን የናጠጡ ሃብታሞችና ታዋቂ ሰዎች በሚስተናገዱበት ሆቴል ህወሃት ለሙዚቃ ዝግጅቱ በብዙ ሚሊዮኖች የሚቆጠር ገንዘብ ያወጣል።
በሌላ በኩል በደቡብ፣ ኦሮምያና ሶማሊያ ክልሎች የረሃቡ ሁኔታ እጅግ አስከፊ ሆኖ መቀጠሉን የሚደርሱን መረጃዎች ያመለክታሉ።