ኢሳት (መስከረም 6 ፥ 2008)
በኢትዮጵያ የመንግስት ስርዓት ውስጥ ህዝባዊ ወያኔ ሃርነት ትግራይ (ህወሃት) ቁልፍ የሆኑ የፖለቲካና ኢኮኖሚያዊ ይዞታዎችን ለመቆጣጠር በኦሮሞና አማራ ብሄር ላይ ሆን ተብሎ የታቀደ ስልታዊ የማግለል እርምጃ ሲወሰድ መቆየቱን በስደት ላይ የሚገኙት የቀድሞ ሚኒስትር አቶ ጁነዲ ሳዶ ገለጡ።
ህወሃት ሲፈፅም በቆየው በዚሁ ስልታዊ ድርጊት በርካታ የኦሮሞና የአማራ የጦር ሰራዊት አባላትና ጀኔራሎች ለእስር መዳረጋቸውንና ከሃገር የኮበለሉ መኖራቸውን ሚኒስትሩ አፍሪካን ኢንተርቴይንመንት በተሰኘ ድረገጽ ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ በጻፉት ጹሁፍ አስፍረዋል።
ፓርቲው ከ10 አመት በፊት ተካሂዶ በነበረው ብሄራዊ ምርጫ ወቅት ያልተጠበቀ አለመረጋጋት እንዲሁም የሃሳብ መከፋፈል ተፈጥሮ እንደነበር ያወሱት የቀድሞ የትራንስፖርት እንዲሁም የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር አቶ ጁነዲን ሳዶ የሁለቱ ብሄረሰቦች እንዲሁም የበርካታ የጉራጌ ብሄር የንግድ ተቋማት በህወሃት ቁጥጥር ስር እንዲሆኑ መደረጉን ገልጸዋል።
ሟቹ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ የነበራቸውን የስልጣን የበላይነት ለማቆየት ሲሉ ማሻሻያዎች እንዳያካሄዱ አድርገው መቆየታቸውን አቶ ጁነዲ ሳዶ በኢትዮጵያ ወቅታዊ ጉዳይ ዙሪያ ባሰፈሩት ጽሁፍ አስነብበዋል።
የጠቅላይ ሚኒስትሩ ሞት ተከትሎ ህግ ከሚፈቅደው ውጭ በህወሃት የበላይነት ቁጥጥር ስር ያለው የኢህአዴግ መንግስት ሁሉም ከአንድ ብሄር የሆኑ 37 ጄኔራሎችን ሹመት ማፅደቁን የቀድሞ ሚኒስትር አውስተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማርያም ደሳለኝ የምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርነት ቦታን እንዲረከቡ ቢደረግም በፖለቲካ ስርዓቱ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ቀጥተኛ ውሳኔ እንዳይኖራቸው ለማድረግ ለመጀመሪያ ጊዜ ሶስት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሮች ሹመት ተከናውኗል ሲሉ አቶ ጁነዲን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ቁልፍ የሆኑ የመከላከያ፣ የውጭ ጉዳዮች እንዲሁም የፖለቲካና የኢኮኖሚ እንቅስቃሴዎች በህወሃት የበላይነት ቁጥጥር ይገኛል ያሉት አቶ ጁነዲን፣ ከአምስት አመት በፊት ከህወሃት እንዲሰናበቱ የተደረጉ ሃላፊዎች በልዩ ሁኔታ እንዲመለሱ መደረጉን አክለው አስታውቀዋል።
ገዢው ፓርቲ እፈጽመዋለሁ ያለውን የማሻሻያ ዕርምጃ ተከትሎ የተወሰኑ የህወሃት ነበር አባላት ከሃላፊነታቸው እንደተነሱ ተደርጎ ለህዝብ ይፋ ተደርጎ እንደነበር ይታወሳል።
ሃገሪቱ የጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊን ሞት ተከትሎ ለውጥ ሊመጣ ይችላል ተብሎ ቢጠበቅም ከለውጥ ይልቅ ኢትዮጵያ ወደ አደገኛ ሁኔታ ውስጥ ገብታለች ሲሉ ለአመታት በተለያዩ የሚኒስትርነትና ሌሎች የሃላፊነት ስራ ላይ አገልግልለው የነበሩት አቶ ጁነዲን ሳዶ በጽሁፋቸው አስነብበዋል።
የአማራና ኦሮሞ ብሄረሰቦች ሆን ተብሎ በተፈጸሙ በደሎች ሰለባ ሆነ መቆየታቸውን ያወሱት ሚኒስትሩ በሁለቱ ክልሎች እየተካሄደ ያለውን ህዝባዊ ተቃውሞ የሚደነቅ እንዳልሆነና ገዢው መንግስት ግድያን ብቸኛ አማራጭ አድርጎ መውሰዱን አክለው አስረድተዋል።
አቶ ጁነዲን ሳዶ ባለቤታቸው አዲስ አበባ ከሚገኘው ከሳውዲ አረቢያ ኤምባሲ መስጊድን ለመገንባት ገንዘብ ተቀብለዋል ከተባለው ድርጊት ጋር እጃቸው አለበት ተብለው ከአራት አመት በፊት ከስልጣናቸው እንዲነሱ መደረጉ የሚታወስ ነው።