ኢሳት (ሃምሌ 6 ፥ 2008)
ህዝባዊ ወያኔ ሃርነት ትግራይ በጎንደር የተነሳውን ህዝባዊ ተቃውሞ ተከትሎ በአማራ ክልል ለሚኖሩ የህወሃት አባላት በተለይም በንግድ ስራ ለተሰማሩት ግለሰቦች የጥንቃቄ እርምጃ እንዲወስዱ ጥሪ ማስተላለፉ ታወቀ።
የህዝባዊ ወያኔ ሃርነት ትግራይ አባላት የሆኑት በንግድ ስራ የተሰማሩ በአማራ ክልል የሚኖሩ ግለሰቦች በመኖሪያ ቤታቸው አካባቢ እንዲሁም በእጃቸው የሚገኙ ጥሬ ገንዘቦችን ወደ ባንክ እንዲያስገቡና ንብረታቸውን እንዲጠብቁ ጥሪ አቅርበዋል።
ከጎንደር ባሻገር በባህርዳርና ደብረማርቆስ ለሚኖሩ የህወሃት አባላት ተመሳሳይ መልዕክት መተላለፉን መረዳት የተቻለ ሲሆን፣ ራቅ ባሉት የአማራ ክልል አካባቢዎች መልዕክቱ ስለመተላለፉ ማረጋገጥ አልተቻለም።
በተለይ በህወሃት የወጣት አደረጃጀት ስር ያሉትና በአማራ አካባቢ በተለያዩ ስራዎች ላይ የሚገኙትን ወጣቶች ንብረታቸውን ከመጠበቅና እንቅስቃሴያቸውን ከመገደብ ባሻገር ያልተለመዱ እንቅስቃሴዎችን ሪፖርት እንዲያደርጉ ለጸጥታ ሃይሎች ድጋፍ እንዲሰጡ ጥሪ እንደቀረበላቸው መረዳት ተችሏል።