ሐምሌ ፲፬ ( አሥራ አራት ) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ከወልቃይት ጠገዴ የአማራ ማንነት ጋር በተያያዘ በሰሜን ጎንደር የተነሳውን ህዝባዊ አመጽ ተከትሎ በአካባቢው የሚታዬው ውጥረት እንደቀጠለ ባለበት ወቅት፣ ህወሃት መራሹ የትግራይ መስተዳድር፣ የኮሚቴ አባላቱን እንዲሁም አጠቃላዩን የህዝብ ንቅናቄውን የሚያወግዙ ሰልፎችን በማዘጋጀት ዋናውን የማንነት ጥያቄ ለማደፋፈን የሚያደርገው ሙከራ አደገኛ ውጤት ይኖረዋል ሲሉ የኮሚቴ አባላቱ አስጠንቅቀዋል።
በአዲ ረመጥ የተካሄደው የተቃውሞ ሰልፍ ህወሃት ራሱ ያሰፈራቸውን ሰዎች በመኪና ጭኖ በማምጣት ያካሄደው ነው የሚሉት የወልቃይት ጠገዴ የአማራ ምንነት የኮሚቴ አባል፣ በአዲ ረመጥ፣ ቃፍታ፣ ጠገዴና ሁመራ የወልቃይት ጠገዴ ወጣቶች ተሰደው ጫካ ውስጥ መኖር መጀመራቸውን ይገልጻሉ። 10 በመቶ የማይሞሉ ሰፋሪዎች 90 በመቶ የሚሆነውን የወልቃይት ጠገዴን ህዝብ ሊወክሉ እንደማይችሉም ይከራከራሉ።
ህወሃት ከጨካ ጀምሬ ሃሰቱን እውነት ብሎ የሚሄድበትን አሰራር በመቀየር ለተነሳው የህዝብ ጥያቄ ህገመንግስታዊ የሆነ መልስ የማይሰጥ ከሆነ፣ ድርጅቱንም ህዝቡንም አደጋ ውስጥ ይጥላል ሲሉ የሚያስጠነቅቁት የኮሚቴ አባሉ፣ ይባስ ብሎ ሰሞኑን የራሳቸውን ሰዎች መሳሪያ እያስታጠቁ እልቂት እንዲፈጠር ለማድረግ እየሞከሩ ነው ብለዋል ። የህዝባዊ ጥያቄው ችቦ የተለኮሰ በመሆኑ ከእንግዲህ አይጠፋም በማለት ተወካዩ አስተያየታቸውን ደምድመዋል።