ህወሃት በመንግስት ወጪ 40ኛ አመቱን ለማክበር ሸርጉድ እያለ ነው

ታኀሳስ (ስምንት) ቀን ፳፻፯ / ኢሳት ዜና :-በከፍተኛ ዝግጅት ይከበራል የተባለው የህወሃት 40ኛ አመት በአል ወጪ የሚሸፈነው ከመንግስት ካዝና መሆኑ በአባል ድርጅቶች መካከል መነጋገሪያ አጀንዳ እየሆነ መምጣቱን የሚናገሩት የኢህአዴግ ምንጮች፣ ከመንግስት ካዝና ለሚወጣው ገንዘብ የተሰጠው ሰበብ  ገጽታ ግንባታ የሚል መሆኑን ገልጸዋል።

ህወሃት በአሉን ከድርጅቱ ካዝና በተለይም የአገሪቱን ሲሶ ሃብት ከተቆጣጠረው ኢፈርት ካዝና መጠቀም እየቻለ፣ ወጪውን መንግስት እንዲሸፍነው ማስደረጉ ለብዙዎቹ አልተዋጠላቸውም። አጠቃላይ ዝግጀቱ ምን ያክል ገንዘብ እንደሚያስወጣ እስካሁን በግልጽ ባይታወቅም፣ እስካሁን እየተደረጉ ባሉ እንቅስቃሴዎች ወጪውን እየሸፈኑ ያሉት የክልሉ መንግስትና የፌደራሉ መንግስት በጋራ ነው።

የካቲት 11 ቀን የሚከበረውን የህወሃት ቀን አስመልክቶ የተመረጡ ጋዜጠኞችና አርቲስቶችን በመንግስት ወጪ  ታህሳስ 13 ቀን 2007 ዓ.ም ወደ ትግራይ ይጓዛሉ። ህወሃት ከበዓሉ አስቀድሞ የትግራይ ክልልን ለማስጎብኘት ያሰበው ከወዲሁ ሰፊ የፕሮፖጋንዳ ስራ ለማከናወን እንዲመቸው በማሰብ መሆኑን ቅርበት ያላቸው ምንጮች ገልጸዋል፡፡