ህወሃት ቁልፍ ዲፕሎማሲ ስልጣኖችን በራሱ አባላት እየሞላ ነው ተባለ

ኢሳት (ሰኔ 9 ፥ 2008)

የህዝባዊ ወያኔ ሃርነት ትግራይ ህወሃት አባላትን ወደ ቁልፍ ዲፕሎማሲያዊ ስፍራዎች የማሸጋገሩ እርምጃ መቀጠሉ ታወቀ። የህዝባዊ ወያኔ ሃርነት ትግራይ አባል የሆኑት ዶ/ር ኃ/ሚካዔል አበራ በብሪታኒያ የኢትዮጵያ አምባሳደር ሆነው የተሾሙ ሲሆን፣ ሌላው የህወሃት አባል አቶ ብርሃነ ኪዳነ ማሪያም በአቶ ግርማ ብሩ ምርት በዋሺንግተን የኢትዮጵያ አምባሳደር ሆነው እንደሚላኩ ምንጮች ለኢሳት ገልጸዋል።

በሲቪል ሰርቪስ ኮሌጅ ፕሬዚደንት ለረጅም አመታት ያገለገሉትና የአቶ አባይ ጸሃዬ የስጋ ዘመድ መሆናቸው የሚጠቀሰው ዶ/ር ሃይለሚካዔል አበራ በብሪታኒያ የኢትዮጵያ አምባሳደር ሆነው ለብሪታኒያዋ ንግስት የሹመት ደብዳቤያቸውን ያቀረቡት ባሳለፍነው ሳምንት መሆኑንም መረዳት ተችሏል።

የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ስራ አስኪያጅ በመሆን በማገልገል ላይ የሚገኙት ሌላው የህወሃት አባል አቶ ብርሃነ ኪዳነማሪያ በዋሽንግተን የኢትዮጵያ አምባሳደር በመሆን አቶ ግርማ ብሩን ይተካሉ ተብሎ እየተጠበቀ ይገኛል። አቶ ግርማ ብሩ አማካሪ ተብለው ወደ አዲስ አበባ እንደሚሄዱም ምንጮች ገልጸዋል።

በኢኮኖሚ ጡንቻዋ እየፈረጠመች ወደ ባለጸጎቹ ሃገራት እየተጠጋች ባለችው ቻይና የኢትዮጵያ አምባሳደር በመሆን በማገልገል ላይ የሚገኙት የህወሃቱ አቶ ስዩም መስፍን መሆናቸውም ይታወቃል።

ከሃገሪቱ ደህንነትና ጸጥታ ጋር በተያያዘ ባሉ ስፍራዎች በደቡብ ሱዳንና ሱማሊያም በአምባሳደርነት የተሾሙትና የሚመሩት የህዝባዊ ወያኔ ሃርነት ትግራይ አባላት እንደሆም ለመረዳት ተችሏል።