ህወሃት/ኢህአዴግ እየተተገበረ ያለውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅን እንዲሽረው ወይም ክለሳ እንዲያደርግበት ሂውማን ራይትስ ዎች ጠየቀ

ኢሳት (ጥቅምት 21 ፥ 2009)

የኢትዮጵያ መንግስት የአለም አቀፍ ህግጋትን በሚጻረረ መልኩ አሁን እየተገበረ ያለውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መመሪያ እንዲሽረው ወይም ክለሳ እንዲደረግበት ሂውማን ራይትስ ዎች ጠየቀ። ድርጅቱ የኢትዮጵያ መንግስት ያወጀው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ግልጽነት የጎደለውና ለበለጠ ሰብዓዊ ቀውስ የሚዳርግ ነው ብሏል።

አሁን ታውጆ ያለው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማንኛውንም ከመንግስት ጋር በአመለካከት የማይስማማ ኢትዮጵያዊ ለ6 ወራት የመናገር ነጻነቱን የሚገድብ ነው ያሉት የአፍሪካ የሰብዓዊ መብት ተመራማሪ ፊሊክስ ሆርን፣ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ለሰራዊቱ ሙሉ ስልጣን በመስጠት ሰላማዊ ተቃውሞ አድራጊዎችን ጭምር መብታቸውን እንዲገደብ የሚያደርግ ነው ብለዋል።

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የመናገርና የመሰብሰብ ነጻነቶችን የሚገድብ መሆኑን የገለጸው ሂውማን ራይትስ ዎች፣ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አለም አቀፍ ህግ የሚፈቅዳቸው ህጎች በሙሉ ወታደራዊ አፈና እርምጃን የሚያሳይ መሆኑን አስፍሯል። በተጨማሪም የአስቸኳይ ጊዜ መምሪያው፣ በማህበራዊ መገናኛ ብዙሃን መረጃ መለዋወጥ፣ ከውጭ አገራት የሚሰራጩ የቴለቪዥን ጣቢያዎችን መመልከት፣ ተቃውሞ ለማሰማት የንግድ ቤቶችን መዝጋት፣ የተቃዋሚ ፓርቲዎች መሪዎች በመገናኛ ብዙሃን እንዳይናገሩ ማገድ አሁን የኢትዮጵያ መንገስት እየወሰዳቸው ያላቸው እርምጃዎችን እንደሆኑ ሂውማን ራይትስ ዎች ባሰራጨው ጥናታዊ ጽሁፍ አስረድቷል።

በኢትዮጵያ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ከታወጀበት ጊዜ ጀምሮ ከ1ሺ 600 ሰዎች በላይ መታሰራቸውን የገለጸው ሪፖርቱ፣ ከ50 ሰዎች በላይ የሚሆኑ ሰዎች የንግድ ድርጅቶቻቸውን በመዝጋታቸው ተይዘው መታሰራቸው በዝርዝሩ አስፍሯል። በቁጥር ያልታወቁ ሰዎች ደግሞ በግፍ መገደላቸውን፣ በጅምላ መታሰራቸውን፣ ቤታቸው መበርበሩንና፣ ንብረታቸው መዘረፉን ሪፖርቱ ገልጿል።

ሪፖርቱ ማንኛውንም ተቃውሞ ያለመንግስት ፈቃድ እንዳይደረግ፣ ፖሊስ ያለ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ ማንኛውንም ሰው እንዲያስር በኮማንድ ፖስት አዋጅ የተፈቀደ መሆኑን ይገልጻል። “ተሃድሶ” በሚል ተቃዋሚ ተብለው የተጠረጠሩትን ሰዎች አካላዊ ቅጣት እንደሚያድርስባቸው በሪፖርቱ ያሰፈረው ሂውማን ራይትስ ዎች፣ ይህም አዋጅ ተቃውሞ በተቀሰቀሰባቸው ክልሎች ብቻ ሳይሆን፣ በሁሉም የአገሪቷ ክፍሎች ተግባራዊ ተደርጎ እንደሚገኝ ተገልጿል።

በአለም አቀፍ ህግ መሰረት፣ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የተወሰኑ መብቶች ሊገደቡ እንደሚችሉ የገለጸው የሰብዓዊ መብት ተቋሙ፣ በኢትዮጵያ መንግስት በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ተግባራዊ ተደርጎ የሚገኘው የመሰብሰብ፣ የመናገር እና የነጻነት መብቶች መገደብ ከአለም አቀፍ ህግ ጋር የሚጻረሩ ናቸው ሲል ገልጿል።

ከህዳር 2008 ጀምሮ እስካሁን ድረስ በመንግስት የተፈጸሙ ወንጀሎች አሁን በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ተካትተል ያሉት ፊሊክስ ሆርን፣ አዋጁን ተንተርሶ የሰብዓዊ መብት ጥሰት መፈጸም የአለም አቀፍ መርህን መጣስ እንደሆነ፣ ሆኖም ግን ውጥረትንና ብሶትን በመጨመር አገሪቷን የባሰ ወደ አዘቅት ይመራታል ሲሉ መናራቸውን በሂውማን ራይትስ ድረ-ገጽ ላይ የወጣው ጽሁፍ ያስረዳል።