ኢሳት (ጥቅምት 29 ፥ 2009)
መቀመጫቸውን በአዲስ አበባ ያደረጉ የውጭ ሃገር ተወካዮች በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ላይ ሲያቀርቡ የቆዩትን ቅሬታ ተከትሎ መንግስት በጉዞ እንቅስቃሴያቸው ላይ የጣለውን እገዳ ማንሳቱን ማክሰኞ አስታወቀ።
የአሜሪካ መንግስትን ጨምሮ የተለያዩ የምዕራባውያን ሃገራት በዲፕሎማቶች ላይ የተጣለውን እገዳ በዕለት ከእለት ስራቸው ላይ ኣሉታዊ ተፅዕኖ ማሳደሩን ሲገልፅ መቆየታቸውን የሚታወስ ነው።
በዲፕሎማቶችን እንቅስቃሴ ላይ የተጣለው እገዳ መነሳቱ ቢነገርም የውጭ ሃገር ተወካዮች የኢንተርኔት አገልግሎት መቋረጥ አሁንም ድረስ ችግር እየፈጠረባቸው መሆኑን አስታውቀዋል።
የአፍሪካ ኮሚሽን ሰኞ ባወጣው መግለጫ መንግስት መሰረታዊ የሰብዓዊ መብቶችን እንዲያከብርና በኢንተርኔት አገልግሎት ላይ የጣለውን እገዳ እንዲያነሳ ጥያቄ ማቅረቡ ይታወሳል።
በኦሮሚያና በአማራ ክልሎች የተቀሰቀሰውን ህዝባዊ ተቃውሞ መንግስት ባለፈው ወር ለስድስት ወር የሚቆይ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ተግባራዊ መደረጉ ይታወሳል።
ይህንን አዋጁ የሰብዓዊ መብት ጥሰትን ለማባባስ አስተዋጽኦ ማድረጉን የተለያዩ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ተቋማት በመግለጽ ላይ ሲሆኑ በርካታ ሰዎች በወታደራዊ ማሰልጠኛ ተቋማትና በሌሎች ጊዜያዊ ዕስር ቤቶች እንደሚገኙ ከሃገር ቤት የተገኘ መረጃ ያመለክታል።