ሰኔ 21 ፥ 2009
በወላይታና በሲዳማ ብሔረሰቦች መካከል ሆን ተብሎ ግጭት ለመፍጠር በአገዛዙ በኩል እንቅስቃሴ እየተደረገ መሆኑ ተገለፀ።
ግጭቱን በሁለቱ ብሔረሰቦች መካከል እንዲፈጠር ምክንያት እየተደረገ ያለው በወላይታና በሲዳማ መካከል በሚገኝው ሁምቦ በተባለ የድንበር ቦታ ይገባኛል ጥያቄ ነው።
ከዚህ ቀደም በድንበሩ ምክንያት በተነሳ ግጭት 13 የወላይታ ተወላጆች ሲገደሉ ከሲዳሞ ሰዎችም በተመሳሳይ ሁኔታ የሰው ሕይወት ጠፍቶ ነበር።
በሁለቱ ብሔረሰቦች መካከል ያለው ውዝግብ ከዚህ በፊት በሽምግልና የተፈታ ቢሆንም እንደገና እንዲቀሰቀስ የአገዛዙ ባለስልጣናት ሕዝብ ሰብስበው የወላይታ ዞን ቦታውን ለሲዳማ መመለስ አለበት እየተባለ መሆኑን የኢሳት ምንጮች ገልፀዋል።
ከቀበሌው 3 ሰዎች እንዲውጣጡ ተደርገው በሶዶ ከተማ በተካሄደው የሕዝብ ስብሰባ ጠቅላይ ሚንስትር አቶ ሐይለማሪያም ደሳለኝ፣ አምባሳደር ተሾመ ቶጋና ሌሎችም የክልል ባለስልጣናት መገኘታቸውንም ለማወቅ ተችሏል።
ለዘመናት ተከባብረውና ተዋደው የሚኖሩ ብሔረሰቦችን ለማጋጨት የተፈለገው የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት መሆኑንም ምንጮቹ ጨምረው ገልፀዋል።
የድንበር የይገባኛል ጥያቄው ከወላይታ ወደ ሲዳማ መዞር አለበት ተብሎ የተሰጠ ሲሆን፣ በ2012 ቀጣይ የኢትዮጵያ ምርጫ የሲዳማ ብሔርሰብ አባላት እንዲመርጡት ለማግባባት መሆኑንም ተናግረዋል።
አገዛዙ ሁለቱን ብሔረሰቦች ለማጋጨት ደባ እየተሰራ ቢሆንም ሕዝብ ጉዳዩን ተረድቶ በንቃት እየተከታተለው መሆኑንም የአካባቢው ምንጮች ለኢሳት ገልፀዋል።