ህብር ስኳር ፋብሪካ እንዲፈርስ ጥያቄ ቀረበ

ኢሳት (ኅዳር 19 ፥ 2009)

ህብር ስኳር አክሲዮን ማህበር እንዲፈርስ ለፍርድ ቤት ማመልከቻ መቅረቡን በሃገር ውስጥ የሚታተሙ ጋዜጦች ዘገቡ።

በማህበሩ ውስጥ ከፍተኛ ድርሽ ያላቸው ከሰባት የሚበልጡ ባለ አክሲዮኖች ለፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ያቀረቡት አቤቱታ እንደሚያስረዳው ፋብሪካውን ለመገንባት ከአባላት መዋጮና እና ከባንክ ገንዘብ ለማግኘት እምነት የነበረ ቢሆም ሊሳካ አልቻለም።

ከአንድ መቶ ሚሊዮን ብር በላይ ከአክሲዮን ሽያጭ የሰበሰበው ህብር ስኳር ከመንግስት ባንኮች ተጨማሪ ብድርና እገዛ ባለማግኘቱ ከተቋቋመ ዘጠኝ አመታት ያስቆጠረ ቢሆንም፣ በመጨረሻ ማህበሩ እንዲፈርስ ክስ ተመስርቶበታል።

ህብር ስኳር አክሲዮን ማህበር በአማራ ክልል በምዕራብ ጎጃም ዞን ጃዊ ወረዳ ጣና በለስ በሚባለው አካባቢ ከ 6ሺ ሄክታር በላይ መሬት በሊዝ የተረከበው ከ3 አመታት በላይ በመንግስት ቢሮክራሲ ምክንያት ከተንገላታና ከተጓተተ እንዲሁም ከፍተኛ ኪሳራ ከደረሰበት በኋላ መሆኑን መዘገባችን ይታወሳል።

ይህንኑ ተከትሎ ከመንግስት እገዛና ድጋፍ እንዲደረግለት ቢጠይቅም ማህበሩን ለማፍረስ በተንቀሳቀሱና በአባላቱ ውስጥ ሰርገው በገቡ የህወሃት ደህንነቶች መስራቾቹና አደራጆቹ በማዕከላዊ መታሰራቸው ይታወሳል።

ከዚሁ ጋር ተያይዞ የማህበሩ አመራሮች በደረሰባቸው ጫና የብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን (ሜቴክ) ጄኔራሎችና ወታደራዊ መኮንኖች ፋብሪካውን እንገነባለን በሚል ባለአክሲዮኖች ሳይፈቅዱ ከኩባንያው 25 ሚሊዮን ብር መወሰዳቸው አይዘነጋም።

ይህም ሆኖ ግን ኢሳት ስለሁኔታው ከዘገበ በኋላ ሜቴክ 25 ሚሊዮን ብሩሩን ለተወሰነ ጊዜ ከተጠቀመበት በኋላ የለምንም ወለድ ለማህበሩ መመለሱን ለማወቅ ተችሏል።

የህብር ስኳር አስኪዮን ማህበር አመራር ቦርድ አባላት በተደጋጋሚ ጊዜ መንግስት ድጋፍ እንዲያደርግላቸው ለጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማሪያም ደሳለኝ ቢያመለክቱም እስካሁን ድረስ ምንም አይነት ምላሽ አለማግኘታቸውን ሲገልጹ ቆይተዋል።

ህብር ስኳር አክሲዮን ማህበር ከተቋቋመ በኋላ በትግራይ ክልል የሚገኘውና በጄኔራል ጻድቃን ገ/ተንሳዔ የሚመራው ራያ ቢራ አክሲዮን ማህበርን ጨምሮ ሌሎች በስርዓቱ የሚደገፉ ኢንዱስትሪ ተኮር ኩባንያዎች ከፍተኛ ገንዘብና ብድር እየተመቻቸላቸው ወደተግባር ገብተው ምርት መጀመራቸው ይታወቃል።