(ኢሳት ዲሲ–ታህሳስ 17/2010)
ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማርያም ደሳለኝ በፖሊስ ታስረው ፍርድ ቤት እንዲቀርቡላቸው አቶ በቀለ ገርባ ፍርድ ቤቱን ጠየቁ።
አቶ ሃይለማርያም በእነ ጉርሜሳ አያኖ የክስ መዝገብ በመከላከያ ምስክርነት በፍርድ ቤት ቢጠሩም ሕጉን አክብረው ግን አልተገኙም።
የጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት አቶ ሃይለማርያም በስራ መደራረብ ለምስክርነት መቅረብ እንዳልቻሉ ለፍርድቤቱ ደብዳቤ ፅፏል።
በዚህ የክስ መዝገብ 4ኛ ተከሳሽ የሆኑት አቶ በቀለ ገርባ ግን አቶ ሃይለማርያምን ለምስክርነት የጠሩት እንደ ማንኛውም ግለሰብ በመሆኑ የጠቅላይ ሚኒስትር ፅ/ቤት መልስ ሊሰጥ አይገባም ብለዋል።
እናም ሃይለማርያም ደሳለኝ የፍርድቤቱን ትዕዛዝ አክብረው የማይገኙ ከሆነ በፖሊስ ታስረው ይቅረቡልኝ ሲሉ ነው የጠየቁት።
ተከሳሾቹ ለቀረበባቸው ክስ የመከላከያ ምስክር እንዲሆኗቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማርያም ደሳለኝን ብቻ አልጠሩም።
የኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት አቶ ለማ መገርሳ፣ የኦህዴድ ፅህፈት ቤት ሃላፊ ዶ/ር ዓብይ አህመድም ለምስክርነት በፍርድ ቤቱ እንዲገኙ በተመሳሳይ ሁኔታ ታዘው ነበር።
ሆኖም ግን አንዳቸውም የፍርድቤቱን ትዕዛዝ አክብረው በፍርድ ቤት አልተገኙም።
ፍርድ ቤቱም አቶ ሃይለማርያም ትዕዛዝ ባለማክበራቸው እስካሁን የወሰደው ርምጃ የለም።
አቃቤ ሕግ ግን ሰውየው ስራ ስለሚበዛባቸው ምስክርነታቸው ይታለፍ ሲል ጠይቋል።
የእነ አቶ በቀለ ገርባ ጠበቆች በበኩላቸው ፍርድ ቤቱ አቶ ሃይለማርያም ምስክር ሆነው እንዲቀርቡ ውሳኔ ያሳለፈ በመሆኑ አቃቤ ሕግ እንደገና ጥያቄ ሊያነሳ አይችል ሲሉ ተከራክረዋል።